ቀጥታ፡

እሴት ተጨምሮበት ለውጭ ገበያ የሚቀርብን የቡና መጠን ለመጨመር እየተሰራ ነው 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 30/2016 (ኢዜአ)፦ እሴት ተጨምሮበት ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የቡና መጠን ለመጨመር ላኪዎችን ለማበረታታት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ገለጸ።

ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከምታገኝባቸው የግብርና ምርቶች መካከል ቡና ቀዳሚ ነው። 

ለአብነትም ባለፉት አሥር ወራት 210 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ቀርቦ 1 ቢሊየን ዶላር መገኘቱን ባለሥልጣኑ ገልጿል።

ኢትዮጵያ  አብዛኛውን ጊዜ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ቡና እሴት ያልተጨመረበት ወይም ጥሬ ቡና  ነው ።  

ይህንንም ከግምት በማስገባት የቡና ምርት ላይ እሴት ጨምሮ በመላክ ከቡና ምርት የሚገኘውን ገቢ ከፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ባለሥልጣኑ አስታውቋል።   

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር)፤ ይህንን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ የአሰራር ሥርዓት ተዘርግቶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል። 

ለአብነትም እሴት ጨምረው ለውጪ ገበያ ለሚያቀርቡ ላኪዎች ከውጭ ለሚያስገቧቸው እቃዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል። 

በዘርፉ እየቀረበ ባሉ ድጋፎች አሁን ላይ እሴት ጨምረው ለውጭ ገበያ በሚያቀርቡ ላኪዎች መካከል መነቃቃት መፍጠሩን አስረድተዋል።  

የላኪዎች ቁጥርም ካለፈው ዓመት በብዙ ቁጥሩ እንደጨመረና የራሳቸው ማኅበር አቋቁመው ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል። 

ከዘርፉ የሚገኘው ገቢም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ጥሬ ቡና የምትልክባቸው በርካታ አገራት ያሏት ሲሆን እሴት ጨምሮ የሚላክ የቡና ምርት ላይም ሰፊ ተቀባይነት ለማግኘት እየተሰራ ነው ብለዋል።  

በቅርቡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ እስያና መካከለኛው ምስራቅ በሚላክ የቡና ምርት ላይ በማጓጓዣ ክፍያ በአንድ ኪሎ ግራም እስከ 1 ነጥብ 50 ዶላር ቅናሽ ማድረጉን ይታወሳል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም