መገናኛ ብዙኃን የአየር ንብረት ለውጥን የህዝብ መሠረታዊ አጀንዳ የማድረግ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙኃን የአየር ንብረት ለውጥን የህዝብ መሠረታዊ አጀንዳ የማድረግ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው
ድሬዳዋ፤ ግንቦት 30/2016(ኢዜአ)፡- መገናኛ ብዙኃን የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ የሚገኘውን ተፅዕኖ ለመቋቋም የአረንጓዴ ልማትን አጀንዳ በማድረግ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ መስራት እንዳለባቸው የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ መርሃ ግብር ዳይሬክተር አሸናፊ ይማም (ዶ/ር) ተናገሩ።
ዳይሬክተሩ ይህን የተናገሩት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድሬደዋ ላይ " አረንጓዴ ልማት-ለዘላቂ ብልፅግና " በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ ውይይት እያካሄደው በሚገኘው መድረክ ላይ ነው።
የሀገራችን ሚዲያዎች የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ የሚገኘውን ተፅኖዎች በዘላቂነት ለመሻገር እየተሰሩ የሚገኙትን ስራዎች በአግባቡ ተንትነው የማሳወቅ ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ሲሉ ገልጸዋል።
እየተሰሩ የሚገኙት የአረንጓዴ ልማቶችን በዕውቀት እና በክላስተር በተደራጀ መንገድ ለህብረተሰቡ የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
በተለይ በአየር ንብረት ለውጥ ሳብያ የሚጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማሻገር እና የችግሩ ተጎጂ ማህበረሰብ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖዎች እንዳይበገር የተጀመሩ ስራዎች ላይ የተቀናጀ ርብርብ እንዲደረግ መትጋት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
"በተለይ በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ እየተገኙ ያሉት መሠረታዊ ጥቅሞች በየፈርጁ ማሳየት አለባቸው፤ ጥቅሞቹ በህብረተሰቡ ባለቤትነት ተጠብቀው በዘላቂነት እንዲጓዝ ማድረግ የሚዲያው ትልቁ ሚና ነው" ብለዋል።
በፓናል ውይይቱ ላይ የተሳተፉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ አቡኔ አለም እንደተናገሩት ፤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በወቅታዊው አለምአቀፍ እና ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ያዘጋጀው የፓናል ውይይት ለቀጣይ የአረንጓዴ አሻራ ስራ ዘመቻ መሠረታዊ ሚና ይጫወታል ።
ይህን መሠረታዊ አጀንዳ የመገናኛ ብዙኃን አንግበውና አጀንዳ ፈጥረው ህዝቡ በአግባቡ ተገንዝቦ ያለበትን የዜግነት ግዴታ እንዲወጣ ለማስቻል ሚናቸው የላቀ መሆኑን ገልፀዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር ስኬት ላይ ሚናቸው እንዲያጠናክሩም አጀንዳ ፈጥረው መትጋት አለባቸው ብለዋል።
"ይህን ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ደግሞ ሁላችንም ቀረብ ብለን ሚዲያዎችን ማገዝና መደገፍ ይገባናል" ሲሉ ገልጸዋል።
የድሬደዋ አስተዳደር የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱ መሐመድ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዜጎች ስለ አየር ንብረት ለውጥ ተገቢውን ግንዛቤ እንዲፈጥሩ የጀመረው የፓናል ውይይት የሚበረታታና መጠናከር ያለበት መሆኑን ገልጸዋል ።
መገናኛ ብዙኃን በየመስኩ በዳበረ ዕውቀትና ንባብ የተሻለ ስራ እንዲያከናውኑ የባለድርሻ አካላት ሚናና ድጋፍ መጠናከር አለበት ብለዋል።
በአረንጓዴ ልማት ላይ ዜጎችን ባለቤት አድርጎ በሙሉ አቅምና ተጠያቂነት ለማንቀሳቀስ ተከታታይ አጀንዳዎችን በሚዲያ ፈጥሮ መስራት ይገባል ያሉት ደግሞ ዶክተር ሮባ ጴጥሮስ ናቸው።
የሚፈለገውን ለውጥ እንዲያመጡ እና ህዝቡ የአረንጓዴ ልማቱ ባለቤት ሆኖ እንዲመራው ለማስቻል የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በየመስኩ ባሉ የሙያ ዘርፎች ዕውቀትና ክህሎት ሊኖራቸው እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
የፓናል ውይይቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል።