ቀጥታ፡

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመመከት የሚያስችል ኢኮኖሚ ለመገንባት የተጀመረውን ጥረት ለማሳካት ርብርቡ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት

ድሬዳዋ፤ ግንቦት 30/2016(ኢዜአ)፦ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመመከት የሚያስችል ኢኮኖሚ ለመገንባት የተጀመረውን ጥረት ለማሳካት ርብርቡ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት "አረንጓዴ ልማት፤ ለዘላቂ ብልፅግና" በሚል ርዕስ በድሬደዋ ያዘጋጀው አገር አቀፍ የፓናል ውይይት በመካሄድ ላይ  ይገኛል።

በፓናል ውይይቱ ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ካቀረቡት ምሁራን መካከል የኢትዮዽያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ እንደተናገሩት ፤ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚን ለመገንባት ስትራቴጂ ዘርግታ የተቀናጀ ጥረት እያደረገች ነው።

በተለይ የአየር ንብረት ለውጥ በግብርና፣ በተፈጥሮ ሃብት እና በጤና ላይ  የሚያመጣውን ከፍተኛ ተፅዕኖ ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። 


 

ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የአዝርእት እና እንስሳት ሃብት ልማትን በየዓመቱ በዕጥፍ ለማሳደግ እያከናወነች ያለቻቸው ተግባራት ፍሬያማ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።

በተለይ ድርቅን እና ድህነትን በመከላከልና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ በአስር አመት ውስጥ የግብርና ምርትን በእጥፍ የማሳደግ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።

እነዚህን ጅምር አበረታች ለውጦች የበለጠ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በተቀናጀ እና በተናበበ መንገድ መስራት ይገባል ብለዋል።

የአረንጓዴ ልማት ዘመቻውም  የአፈር ለምነትን ይጨምራል፤ የአፈርን ጤንነት በዘላቂነት ያሳድጋል ይህም ምርት እና ምርታማነት እንዲያድግ ያስችላል ብለዋል።

በተጨማሪም የውሃ ሃብትን በቁጠባ በዘላቂነት ለመጠቀምና ለማስተዳደር ከማስቻሉም ባሻገር በቤተሰብ ደረጃ የገቢ መጠን እንዲጨምር አስችሏል ሲሉ ገልጸዋል።  

የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በተስፋፋ ቁጥር በምንተክላቸው ተክሎች መጠን ገቢ ለማግኘት ያግዛል ፤ ለልጆቻችን የተሻለች አገርን ለማስተላለፍ ያስችለናል ብለዋል።


 

ሌላው ጥናታዊ ፅሁፍ  አቅራቢ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ አየር ንብረት ለውጥ ተቋቁሞ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር  ዶክተር ከፈለኝ ጌታሁን በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በተቀናጀ መንገድ በመተግበር  በአየር ንብረት ለውጥ ሳብያ በምስራቅ አፍሪካ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችንና ተጽዕኖን በትኩረት መከላከል እንደሚገባ  ተናግረዋል።

በተለይ በአየር ንብረት ለውጥ ሳብያ የጎርፍ አደጋ፣ የጤና፣ የሰላም እና የድህነት ችግሮች ሊገጥሙ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል።

እነዚህን ችግሮች በተቀናጀ መንገድ የመከላከያ እና የመቀልበስ ጅምር ስራዎችን ተቋማዊ እና በጥናት ላይ በተደገፈ መንገድ የተጀመሩ ተግባራት ላይ በመረባረብ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ይገባል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም