ቀጥታ፡

የአካባቢ ብክለት ለመከላከል ሕዝብን ያሳተፈ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 30/2016(ኢዜአ)፦ የአካባቢ ብክለት በሀገሪቱ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከል ሕዝብን ያሳተፈ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ እየተሰራ መሆኑ ተመላከተ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ብሎም በኢትዮጵያ የልማት እንቅስቃሴ ላይ ሥጋት እየሆኑ ከመጡ ተግዳሮቶች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ መዛባት ይጠቀሳል።

ይህ ዓለምን እየፈተነ ያለውን ችግር ለመከላከል የተለያዩ ሀገራት የአካባቢ ብክለትን ለመታደግ የተለያዩ ተግባራትንና እርምጃዎችን ሲወስዱ ይስተዋላል።

በኢትዮጵያም የአካባቢ ብክለትን በመግታት ለሰው ልጆች ምቹ የአኗኗር ሁኔታን ለመፍጠር መንግሥት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።

ከእነዚህም ውስጥ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርና የወንዝ ዳርቻ ልማትን ማንሳት ይቻላል።

ከዚህም በሻገር በአሁኑ ወቅት "ብክለት ይብቃ፤ ውበት ይንቃ" በሚል መሪ ኃሳብ ሀገር አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ንቅናቄ በመከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል።

ይህንንም መነሻ በማድረግ አዜአ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ የዘርፉ ተዋናዮችን የሀገሪቱን ከአካባቢ ብክለት ለመታደግና የአካባቢ ጥበቃ ንቅናቄ የታለመለት አላማ እውን እንዲሆን እያደረጉ ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተ አነጋግሯል።

በኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሰይፈዲን መሃዲ የአካባቢ ብክለት ለመከላከል በክልሉ የሚገኙ ደኖችን የመጠበቅና የተፋሰስ ልማት ሥራ በስፋት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ሥራን ከምንጊዜውም በላይ አጠናክሮ በመሥራት ሀገሪቱን ከአየር ንብረት ለውጥ ችግር መታደግ ይኖርብናል ሲሉ ገልጸዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የደን አካባቢ ጥበቃ የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ አስራት ገብረማሪያም(ዶ/ር) በበኩላቸው ክልሉ የተፈጥሮ ኃብት ባለቤት ነው።

ይህንን የተፈጥሮ ኃብት ለመጪው ትውልድ በተገቢው ጠብቆ ማቆየት ያስፈልጋል ብለዋል።

በክልሉ የሚገኙ የተፈጥሮ ኃብቶችን ከጉዳት ለመጠበቅና ዘላቂነታቸውን ለማረጋገጥ ማኅበረሰቡ በእኔነት ስሜት እንዲጠብቃቸው የሚያስችል ሥራ በመሥራት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

ከተማዋን ከሚያጋጥሟት ተፈጥሯዊ አደጋዎች ለመከላከል ቀጣይነት ያለው የተፋሰስ ልማት ሥራ ሕዝቡን በንቃት ባሳተፈ መልኩ በመስራት ላይ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ የደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን ኃላፊ አብዱ መሀመድ ናቸው።

መንግሥት የአካባቢ ብክለት እያሳደረ ያለውን ሀገራዊ ተጽእኖ ለመቅረፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት መሰረት በየአካባቢያቸው ”ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ኃሳብ በዘርፉ ላይ ለውጥ ሊያመጡ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የተጀመረውም ንቅናቄ ውጤታማ እንዲሆን ሕዝብን በባለቤትነት ያሳተፈ ሥራ በመሥራት ላይ መሆናቸውን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም