ኢዜአ የኢትዮጵያውያን የጋራ አጀንዳ የሆነውን የአረንጓዴ ልማት ግቡን እንዲመታ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ የኢትዮጵያውያን የጋራ አጀንዳ የሆነውን የአረንጓዴ ልማት ግቡን እንዲመታ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል
ድሬዳዋ ፤ ግንቦት 30/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያውያን የጋራ አጀንዳ የሆነው የአረንጓዴ ልማትን ማፋጠን የተረጂነትን ስነ ልቦናን በመጠየፍ ብልፅግናን እውን ለማድረግ የሚያስችል መሳሪያ በመሆኑ ኢዜአ ለመርሃ ግብሩ መሳካት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢዜአ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ ገለጹ።
"አረንጓዴ ልማት ለዘላቂ ብልጽግና" በሚል መሪ ሃሳብ ኢዜአ ያዘጋጀው የፓናል ውይይት በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የፌዴራልና የድሬዳዋ አስተዳድር አመራር አባላት፣ የአየር ንብረት ለውጥና አረንጓዴ ልማት ላይ በማተኮር የሚሰሩ ተቋማት ተወካዮች፣ የመገናኛ ብዙሃን አመራር አባላት፣ የዘርፉ ምሁራንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ አጀንዳ ችግኝ በማዘጋጀትና በመትከል፣ ጎርፍን በመከላከልና በረሃማነትን በማስወገድ ከሚከናወን የአካባቢ ጥበቃ ስራ በላይ በሁሉም ዘንድ ባህል እየሆነ መጥቷል።
በዚህም የችግኝ ተከላ አገር አቀፍ የማስጀመሪያ ፕሮግራም ኢትዮጵያውያን የሚናፍቁት ልዩ ቀን እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል።
በተለይ ከለውጡ ወዲህ ይህ የንቅናቄ መርሃ ግብር ሁሉም እንዲሳተፍበት ለማስቻል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) አርአያ በመከተል ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በአንድነት የአረንጓዴ አሻራን ጉዳይ የጋራ መሰባሰቢያ አድርገውታል ብለዋል።
ይህም ተረጂነትን በመጠየፍ ብልፅግናን እውን ለማድረግ የሚያስችል መሳሪያ መሆኑን ገልፀዋል።
ባለፈው የክረምት መርሃ ግብር “ነገን ዛሬ እንትከል!” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው የችግኝ ተከላ በአንድ ቀን ብቻ ከ500 ሚሊየን ችግኝ በላይ መተከሉ፣ ኢትዮጵያውያን በአገራዊ የጋራ ጉዳዮቻቸው አንድ ሆነው በመቆም የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚከናወነውን በጎ ስራ ለማሳካት ያላቸውን ትብብር፣ ህብረትና አንድነት ያሳያል ብለዋል።
ዘንድሮም ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፣ በብሄራዊ ደረጃ ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ከወዲሁ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
የአረንጓዴ ልማት ስራ ተስማሚ ስነ ምህዳር ለትውልድ ለማቆየት፣ የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም፣ በግብርናው ዘርፍ ደግሞ የሰብልና እንስሳት ሀብት ልማትን ለማሳደግ፣ ጎርፍና መሰል የድርቅ ተፅዕኖዎችን ለመከላከል እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ከዚህ በላይ የተረጂነት ስነ ልቦናን በማስወገድ ለራስ በራስ የመኖርን ጀግንነት እንደሚያጎናፅፍ ገልፀዋል።
መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያውያን የጋራ አጀንዳ የሆነው አረጓጓዴ ልማት ለዘላቂ ብልጽግና የሚኖረውን ፋይዳ በማስረፅ ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ከራሷ ባለፈ ለጎረቤቶቿ ብሎም ለዓለም እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦና አርአያነቷን በሚገባ ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል።
ኢዜአም ለዚህ ሀገራዊ አጀንዳ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት፣ በተለይ ከተረጂነት የወጣ ስነ ልቦናን በመገንባት በልማት የማደግና የመለወጥ ብሂልን በማስረፅ በኩል መንግስት የጀመረውን ጥረት ህዝብ የሚወያይበት አጀንዳ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።
ኢዜአ በዚህ ዓመት በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች ካዘጋጃቸው 13 የፓናል መድረኮች በተለየ ይህን 14ኛ የፓናል መድረክ አረንጓዴ ልማት ላይ ያተኮረ እንዲሆን አድርጓል ሲሉ ገልጸዋል።