"ቢስት ባር" - ያንዱ ላንዱ የመተሳሰብ ስብዕና መገለጫ

             "ቢስት ባር" -   ያንዱ ላንዱ የመተሳሰብ ስብዕና መገለጫ

                                                                በቀደሰ ተክሌ

ታላቅ የሚከበርበት፣ ፍቅር ለምልሞ አብሮነትን የሚደምቅበት፣ በዝናብ አብቅሎ ቤታቸውን በእህል ለሞላው ፈጣሪ ቤንቾች ምስጋና የሚያቀርቡበት በዓል- "ቢስት ባር"። 

"ቢስት" ማለት የመጀመሪያ ወይም በኩር ማለት ሲሆን በክረምቱ የተዘራ እህል ደርሶ የመጀመሪያውን ፍሬ የሚቀምሱበት መሆኑን ያመለክታል። "ባር" ማለት ደግሞ በዓል የሚል ቀጥተኛ ትርጉም አለው። ታዲያ ይህ የመጀመሪያ እህል ከመቅመስ ጋር ተያይዞ የሚከበረው በዓል ከዛም ከፍ ያለ ትርጉም ያለው ነው። በቤንቾች ዘንድ ለሰው ልጅ ተገቢውን ክብር መስጠት ባህል ነው። ክብር ሲሰጥ ከጣት እንኳን ረጅምና አጭር አለ የሚል ብሂልን አስደግፈው ታላቅን እንደ ታላቅነቱ ከፍ የማድረግ ልምዳቸው የጎላ ነው።

በ"ቢስት ባር" ከመጀመሪያው እህል የተዘጋጀውን ምግብም ሆነ መጠጥ የመጀመሪያ ልጅ ወይም ታላቅ ሳይቀምስ ሌሎች ታናናሾች ወደ አፋቸው አያደርሱም። የ"ቢስት" በዓል ለልጆች መከባበርን በማስተማርና የሥርዓቱ ሰንሰለትን ከቀጣይ ትውልድ ጋር በማስተሳሰር የሚከበር በዓል ነው። የደረሰውን እህል የበኩር ልጅ እንደቀመሰ በእድሜ ደረጃ ከታላቅ እስከ ታናሽ በተራ ይደርሳል። ከዚህ በኋላ የተዘጋጀው ምግብ ከቤተሰብ አልፎ ለጎረቤት ተዳርሶ ሐሴት ይደርግበታል። በቤንች የመጀመሪያን እህል ለብቻ መቅመስ ነውር ነው። ይህም ህዝቡ ለአብሮነት ቦታ እንዲሰጥ ያስቻለ ቱባ ባህል ነው። 

የ"ቢስት ባር" ሌላኛው ደማቅ ገጽታ መደማመጥ ነው። ሰው ካልተደማመጠ አይከባበርም፤ ካልተከባበረ ደግሞ አብሮነት አይዘልቅም፤ አብሮነት ከሌለ በመራራቅ ውስጥ በሚፈጠር ክፍተት ሰላም ይደፈርሳል። ለዚህም ቤንቾች ለመደማመጥ ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። ባላባቶች በቢስት ባር የልማት ሥራና ሌሎች ጉዳዮች ላይ መመሪያዎችን በምርቃት አዋዝተው ያስተላልፋሉ። ሌሎች ጆሮ ሰጥተው ያዳምጣሉ ድርጊቱን ተቀብለው በነጋታው ይተገብራሉ።

ለ"ቢስት" በዓል የተጣላን ሊያስታርቅ የተቀመጠ ሽማግሌ ብዙ አይደክምም። በሁለቱ ጠበኞችና በሽማግሌዎች መካከል መከባበርን መሠረት ያደረገ መደማመጥ አለና። የተደማመጠ ደግሞ መግባባቱ ስለማይቀር በሽማግሌ ምክር ራሳቸውን በፍቅር ያድሳሉ። ወዲያው ታርቀው አንድ ይሆናሉ፤ "ቢስት ባር"ን በወንድማማችነት ያከብራሉ።

የቤንች ልጆች በዓመት አንድ ጊዜ ከሌሊት ጨረቃና ከዋክብት ጋር ደስታቸውን የሚጋሩበት ልዩ ቀን "ቢስት ባር" ነው። ለቢስት ባር የተዘጋጀውን ምግብ ቀምሰው ቦርዴውን ፉት እያደረጉ ከባላባቶች ጋር የምስጋና ሥነ ሥርዓትን እንዳከናወኑ ወደ ውጭ ወጥተው በጨረቃ ብርሃን ይጨፍራሉ። በፍጹም ልብ ተዋደው በአንድ ቀዬ ተሰበስበው ያለ ልዩነት ፌሽታ የሚያደርጉበት የአብሮነት በዓል ነው- ቢስት ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቤንች ሸኮ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ኮይካ እንደሚሉት የ"ቢስት ባር" የሕዝቦችን የእርስ በእርስ ትስስር የማጎልበት አቅም ያለው ኩነት ነው። በበዓሉ ወቅት የሚፈጸሙ ባህላዊ ክዋኔዎች ከበዓል ያለፈ ትርጉም ያላቸው ናቸው። ለአብነትም በቢስት ባር የተቀያየመ ይታረቃል፣ ያጠፋ ቢኖር ምሕረት አግኝቶ ፍቅር አንድነት ይሰፍናል ይላሉ። የዚህ ሥነ ሥርዓት ክዋኔ ባለቤት የሆኑ የጎሳ መሪዎችና ባለባቶች ስብከታቸው ፍቅር፣ ምክራቸው በጎነት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የቢስት ባር ስለተደረገ ነገር ምስጋና ማቅረብን የሚያስተምር እንደሆነም ነው አቶ ጌታቸው የሚናገሩት። አርሶ አደሩ ወጥቶ ወርዶ የዘራው ሰብል እንዲበቅል ዝናብን ሰጥቶ፤ በዝናቡ ከበቀለ በኋላም ፀሐይን አፈራርቆ አዝመራን በምርት ለሚሞላ ፈጣሪ ምስጋና መስጠት የበዓሉ መሠረት ነው ይላሉ። ያገኙትን ምርት ከመጠቀማቸው በፊት ተሰብስበው ያመሰግናሉ። በምስጋናው ሥነ ሥርዓት ለሀገር ሰላም ለቀጣዩ አዝመራ መልካምነትና ስለቤተሰብ ጎረቤት ጤንነት ልመና እንደሚቀርብ ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው እንደሚሉት የ"ቢስት ባር" በውስጡ የያዛቸውን እምቅ ሀገር በቀል እውቀቶች ያሁኑ ትውልድ ቢማር ሰላምና ፍቅር፤ መቻቻልና መከባበር በልጽጎ የሕዝቦች አንድነት ይጠነክራል። ለዚህም ተቋርጦ የነበረውን የ"ቢስት ባር" በዓል አከባበር በተለያዩ ጥናቶች በማስደገፍ በዓሉን ዳግም ለማስጀመር ብዙ ሥራ መሠራቱን ጠቁመዋል።

ከቤንች ባላባቶች መካከል መርቴት ሻሽ በሰሜን ቤንች ወረዳ የኡፅቅን ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። በዓሉ ከተቋረጠ ረጅም ዓመታት በኋላ በህይወት እያሉ በመከበሩ መደሰታቸውን ተናግረዋል። በተለይ በዓሉ ሰብዓዊነትን ከፍ አድርጎ የሚከበር መሆኑን ጠቅሰው ሳይበረዝ እንዲከበር በዝግጅት ሥራው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።

የጥንት ባህላዊ ሥርዓቶቻችን በሀገር በቀል እውቀቶች የተቃኙ በመሆናቸው ለሰላምና ለአብሮነት ያላቸው ፋይዳ የጎላ እንደሆነ አንስተው በዓሉ ከምስጋናና እህል መቅመስ ባለፈ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ነው ሲሉም ገልጸዋል። ከቢስት ባር ማግስት የሥራ መመሪያ ተሰጥቶ ለቀጣዩ አዝመራ ሰፊ ዝግጅት የሚደረግበት እንደሆነም አስረድተዋል።

የ"ቢስት ባር" እሴቶች ዛሬ ላይ ላለው ትውልድ እጅግ አስፈላጊ ናቸው። ምክንያቱም የሰላም መሠረቶችን ጠንቅቆ ማወቅና መተግባር የሚያስችል የመከባበርና የአብሮነት ሥርዓትን የያዘ ነውና። የትናንት መልካም ተሞክሮዎችን ከባህል እልፍኝ እየቀዱ መጠቀም ተገቢ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በዓሉ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የአንድነት ተምሳሌት ሆኖ እንዲቀጥል ከሌሎች ባላባቶችና የሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት አጠናክሮ ለማስቀጠል ጥረት እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

በዓሉ አብሮነት የሚንጸባረቅበት በመሆኑ ሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በአንድነት ያከብሩታል። ከማክበርም አልፎ የዝግጅት ምዕራፉን ጭምር በሀሳብና በገንዘብ ጭምር ደግፈዋል። ይህ እውነተኛ ወንድማማችነትን የሚያረጋግጥ በጎ በዓል ግንቦት 29 እና ሰኔ 01 ቀን 2016 ዓ/ም በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ደምቆ ይከበራል። የ"ቢስት ባር" ከበዓል ያለፈ የመተሳሰብ ባህል በአካባቢው የሚሰፍንበት እንደሆነም ጠቅሰዋል። ለአርሶ አደሩ እህል እኩል የማይደርስበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። በዚህን ጊዜ ቀድሞ የደረሰለት ለሌላው ጎረቤቱ ያካፍላል። አዲሱን እህል አብሮ በማጣጣም የጋራ ደስታ ይፈጥራሉ። ይህም ቢስት ባር ያለው ለሌለው ማዕድ የሚያጋራበት የጥንት ሥርዓት መያዙን ያመለክታል።

ሕዝብን በፍቅር የሚያስተሳስር እሴትን በጉያው ያቀፈው የቢስት ባር የቤንቾች መነሻ በሆነው "ዣዥ" በሚባል ቀበሌ ግንቦት 30 ይከበራል። በማግስቱ ሰኔ 01 ደግሞ በዞኑ መቀመጫ ሚዛን አማን ከተማ በአማን የቀድሞ አየር ሜዳ ላይ በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ታጅቦ ይከበራል።

"ቢስት ባር" የኢትዮጵያ አንዱ ቀለም ነው፤ ትናንት ላይ ቀደምቶች ያጌጡበት የፍቅር ሸማን የፈተለ፤ አብሮነት ዘርቶ ሰላምን ያበቀለ፣ ሰው ሰው የሚሸት የትውልድ አሻራ። ዛሬም ያ እሴት ከአካባቢው አልፎ ለሀገር እንዲተርፍ መሥራት ያስፈልጋል።  ያ መከባበር ዛሬም በሁሉም አቅጣጫ ትውልዱ ላይ መስፈን አለበት። ያ ያለስስት ከጓዳና ጎተራ ሰፍሮ ለሌለው የሰጠ እጅ በሁላችንም ልብ ሰርጾ ዛሬም አቅመ ደካማን ማጉረስ አለበት በማለት ጉዳዬን ቋጨሁ።

መልካም "ቢስት ባር"!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም