ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከጊኒ ቢሳው ጋር ነጥብ ተጋርታለች

አዲስ አበባ፤ግንቦት 29/2016(ኢዜአ)፦በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ ከጊኒ ቢሳው ጋር ባደረገችው ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይታለች።

በ'ስታዲዮ ናሲዮናል 24 ዲ ሴቴምብሮ" ስታዲየም ማምሻውን በተካሄደው ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከባለሜዳው ቡድን የተሻለ የግብ እድሎችን መፍጠር ቢችልም ሊጠቀምበት አልቻለም።

ከእረፍት መልስ ተቀይሮ የገባው የወላይታ ድቻው የፊት መስመር ተሰላፊ ቢኒያም ፍቅሩ ያመከነው ግልጽ የግብ እድል ተጠቃሽ ነው።

በጨዋታው ወቅት በነበረው ከ30 ዲግሪ ሴልሸየስ በላይ ሙቀት የቡድኖቹን ተጫዋቾች የፈተነ ሁኔታ ነበር።

ውጤቱን ተከትሎ በምድብ አንድ የምትገኘው ኢትዮጵያ ሁለት ነጥብ ይዛ በነበረችበት 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ጊኒ ቢሳው በ5 ነጥብ በጊዜያዊነት ከነበረችበት 3ኛ ደረጃ ወደ 2ኛ ከፍ ብላለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አራተኛ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታውን ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ሞሮኮ ላይ ከጅቡቲ ጋር ያከናውናል።

በምድብ አንድ ሌላኛው መርሐ ግብር የምድቡ መሪ ግብጽ ከቡርኪናፋሶ ጋር ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ በካይሮ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም