የመንግስት ተቋማት የመልካም አስተዳደር ስራን በእቅዳቸው በማካተት ለተፈጻሚነቱ በትኩረት መስራት አለባቸው - አቶ እውነቱ አለነ - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት ተቋማት የመልካም አስተዳደር ስራን በእቅዳቸው በማካተት ለተፈጻሚነቱ በትኩረት መስራት አለባቸው - አቶ እውነቱ አለነ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2016(ኢዜአ)፦ የመንግስት ተቋማት የመልካም አስተዳደር ስራን በእቅዳቸው በማካተት ለተፈጻሚነቱ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በ2015 በጀት ዓመት የተሻለ የመልካም አስተዳደር አፈጻጸም ለነበራቸው ስድስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እውቅና ሰጥቷል፡፡
በእውቅና መርሃ ግብሩ ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የምስክር ወረቀትና የዋንጫ ሽልማት የተበረከተ ሲሆን ከአራት እስከ ስድስት ለወጡት ደግሞ የእውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡
ውጤታማነት፣ ተጠያቂነት፣ ፍትሃዊነት፣ ግልጸኝነትና የህግ የበላይነት የመልካም አስተዳደር የምዘና መስፈርቶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በዚህም ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ትምህርት ሚኒስቴርና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ ሶስት በመውጣት የዋንጫና የምስክር ወረቀት ተሸላሚ ሆነዋል።
በእውቅና መርሃ ግብሩ የተገኙት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ፤ መንግስት በተለይ ከለውጡ ወዲህ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በርካታ ተግባራትን በማከናወኑ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በመልካም አስተዳደር ዘርፎች እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል፡፡
በዚህም የመንግስት ተቋማት በ2016 በጀት ዓመት የመልካም አስተዳደር አፈጻጸማቸው ተገምግሞ ውጤት እንደሚሰጥም ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም ተቋማቱ የመልካም አስተዳደር ስራን በእቅዳቸው በማካተት ለተፈጻሚነቱ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ በበኩላቸው፤ የተቋማትን የመልካም አስተዳደር አፈጻጸም ደረጃ በመለካት ማበረታታት ወይም የማሻሻያ ሃሳብ መስጠት ከተቋሙ ተልዕኮዎች መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የተቋማትን የመልካም አስተዳደር ቁመና መለካት ያስፈለገው የተሻለ የሰሩትን ለማበረታታት በአንጻራዊነት ዝቅ ያለ አፈጻጸም ያሳዩትን ደግሞ የማሻሻያ ሃሳብ ለመስጠት መሆኑን አመልክተዋል፡፡