የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ኩባንያዎች ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር ተደራሽነቱን ለማስፋት እየሰራ ነው-አቶ መስፍን ጣሰው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ኩባንያዎች ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር ተደራሽነቱን ለማስፋት እየሰራ ነው-አቶ መስፍን ጣሰው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ከዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ኩባንያዎች ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር ተደራሽነቱን ለማስፋት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
በፈረንሳይ በአቪዬሽን ኤሮስፔስና፣ ኤርፖርቶች መስክ የሚሰሩ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አመራሮች ጋር በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ በአዲስ አበባ ምክክር እያካሄዱ ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት፤ አየር መንገዱ ተግባራዊ እያደረገ በሚገኘው ስትራቴጂክ እቅድ መሰረት በአቬዬሽን ዘርፍ ውጤታማ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
አዳዲስ መዳረሻዎችን ማስተዋወቅ፣ ያሉትን የአውሮፕላን ቁጥሮች መጨመር እንዲሁም የአቬሽን መሰረተ ልማቶችን መገንባት ደግሞ አየር መንገዱ እያከናወናቸው ካሉ ስራዎች መካከል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ከዓለም የአቪዬሽን ኩባንያዎች ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር ተደራሽነቱን ለማስፋት እየሰራ መሆኑን አንስተው፤ ከነዚህም ውስጥ በፈረንሳይ የሚገኙ የዘርፉ ኩባንያዎች ተጠቃሾች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይ ከኤር-ባስ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ጋር አየር መንገዱ በቅርበት እየሰራ ሲሆን በቅርቡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኩባንያው የአውሮፕላኖች ግዥ ትዕዛዝ መፈጸሙን ገልጸዋል።
ይህም ብቻ ሳይሆን አየር መንገዱ ከፈረንሳይ ኩባንያዎች ጋር በኤሮ-ስፔስ፣በአውሮፕላን መለዋወጫ ማምረቻና ሌሎችም መስኮች በጋራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለማስገንባት በሂደት ላይ ያለው የአዲስ የኤርፖርት ከተማ ፕሮጀክት የመጀመሪያውን ጥናት ያደረገው የፈረንሳይ ኩባንያ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ይህም አየር መንገዱ ከፈረንሳይ የአቪዬሽን መስክ ኩባንያዎች ጋር ያለው ግንኙነት እያደገ መምጣቱን የሚያመላክት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣የአውሮፕላን ኢንጂንና የተለያዩ የአውሮፕላን መለዋወጫዎችን ከፈረንሳይ ኩባንያዎች እንደሚገዛም ነው የተናገሩት፡፡
በቀጣይም አየር መንገዱ ከፈረንሳይ ኩባንያዎች ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ያለውን ትስስር አጠናክሮ መቀጠል ይፈልጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ በበኩላቸው፣ ሁለቱ ሀገራት ያላቸው ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው መጠናከር ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የዛሬው መድረክ የፈረንሳይ የአቪዬሽንና ኤሮ ስፔስ ዘርፍ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ጋር የጀመሩትን ትስስር አጠናክሮ ማስቀጠል ላይ ትኩረቱን ያደረገ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየጊዜው እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በአቪዬሽን መስክ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ሰፊ እድሎች መኖራቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
ኩባንያዎቹ፣ በኤሮ ስፔስ ማኑፋክቸሪንግ፣በፕሮጀክት ግንባታና አጠቃላይ በኤርፖርት አስተዳደር ዘርፍ ያላቸውን ልምድና ተሞክሮ በመጠቀም ከአየር መንገዱ ጋር በጋራ እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
በተለይ በአዲሱ የኤርፖርት ከተማ ግንባታ ላይ የፈረንሳይ ኩባንያዎች ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
መድረኩ በኢትዮጵያ ፈረንሳይ ኤምባሲ በኩል የተዘጋጀ ሲሆን ምክክሩ እስከ ነገ የሚቀጥል መሆኑም ታውቋል።