ቀጥታ፡

የተሟላ ሀገራዊ ነጻነትን ለማረጋገጥ ከተረጂነት አስተሳሰብ መውጣትና ምርታማነትን የማሳደግ አርበኝነት ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2016(ኢዜአ)፦ የተሟላ ሀገራዊ ነጻነትን ለማረጋገጥ ከተረጂነት አስተሳሰብ መውጣትና ምርታማነትን የማሳደግ አርበኝነት ያስፈልጋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አሳሰቡ።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮች፣ የፌደራልና የክልል ተቋማት ኃላፊዎች በተገኙበት  መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።

በስብሰባው ከ10 ዓመታት በኋላ ተሻሽሎ የጸደቀው የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲና የ2016 የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት አፈጻጸም በዝርዝር ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ተመስገን ጥሩነህ በመክፈቻ ንግግራቸው፥ በፖሊሲው ሀገርን ከተረጂነት የማላቀቅ አቢዮትን የመቀስቀስ ዓላማ መቀመጡን ገልጸዋል።


 

ሰውሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች አይቀሬ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ከዚህ አኳያ አደጋን በራስ አቅም የመቋቋምና ምላሽ የመስጠት ቁመና መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ይህንን ለማሳካት የሚያስችሉ የሌማት ትሩፋት፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የበጋ መስኖ ልማትን ጨምሮ ሁሉንም አቅሞች በውጤታማነት ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቅሰው፥ ከሁለም በላይ ልመናን የመጸየፍ የባህል ለውጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም አዲሱ ፖሊሲ ዓይነታቸውና ውስብስብነታቸው እየጨመሩ የመጡ አደጋዎችን በራስ አቅም መቋቋምን ያለመ ነው ብለዋል።


 

የአደጋ ስጋት  አመራር መርህና አይበገሬነት ግንባታ ላይ ሁለንተናዊ አመራር መስጠት፣ የቅድመ አደጋ፣ የአደጋ፣ የድህረ አደጋ ምዕራፎችን በሁሉም የአስተዳደር እርከኖች በመተንተን ለአደጋ የማይበገር ሀገርና ማህበረሰብ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአደጋ ስጋት ቅነሳ፣ በሁሉም መዘጋጀት፣ ሀብት ማሰባሰብና አቅምን ማሸጋገር እና ሰብዓዊ ድጋፍን በዘላቂነት በራስ አቅም መቻል የፖሊሲው ትግበራ የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው ብለዋል።

በውይይቱ ከተሳተፉ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች መካከል የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ፥ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም የመሸፈን ሀገራዊ ግብን ለማሳካት  ትልቅ ስራ ይጠይቃል ነው ያሉት።


 

በሶማሌ ክልል የተረጂነት የአስተሳሰብ ችግር መኖሩን ጠቅሰው፥ የተረጂዎችን ቁጥር የማጋነን ሁኔታ እንደነበረና በአሁኑ ወቅት ግን የማጥራት ስራዎች በማከናወን ቁጥሩ መቀነሱን ገልጸዋል።

በቀጣይ ከጥገኝነት ለመላቀቅ በሚደረገው ጥረት የአደጋ ምላሽ የእርዳታ ፖለቲካን የሚፈልጉ ኃይሎች በተዛባ መልኩ ሊንቀሳቀሱ እንደሚችሉ በማሰብ መዘጋጀት ተገቢ  መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው፥ እንደ ሀገር በሁሉም መስክ ከጥገኝነት ለመላቀቅ የሚያስችል የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ተግባቦት እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ለዜጎች የአደጋ ጊዜ እህል ክምችትን ከማዘጋጀት ጎን ለጎን ለአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የህልውና መሰረት ለሆኑት እንስሳት መኖ ዝግጅትም ትኩረት መስጠት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ህዝብን ባሳተፈ ቁርጠኛ አመራር ከተረጅነት የመላቀቅ ጉዞን እናሳካዋለን ነው ያሉት።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፥ የተሟላ ሉዓላዊነት ለማግኘት የተጀመረውን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት ምርታማነትን የማሳደግ የአርበኝነት ንቅናቄ በክልል መጀመሩን ገልጸዋል።


 

በበጋ ስንዴ ልማት የተመዘገበው የታሪክ እጥፋት ሰብዓዊ ድጋፈን በራስ አቅም በመሸፈን መድገም እንደሚያስፈልግም ነው የጠቆሙት።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በሰጡት ማጠቃለያ፥ ሁሉም ክልሎችና ተቋማት የተረጂዎችን ትክክለኛ ቁጥር እንዲያጠሩና ወደ ዲጅታል አሰራር እንዲገቡ አሳስበዋል።

አደጋዎች በማንኛውም ሁኔታ ሊከሰቱ እንደሚችሉ በመገንዘብ  የራስን ሰብዓዊ ችግር በማህበረሰባዊ የመረዳዳት ባህል እና በሀገራዊ የልማት ጥረቶች በመቋቋም የተሟላ ነጻነትን ማወጅ ተገቢ ነው ብለዋል።

ለዚህም የጋራ ተግባቦትን መፍጠር፣ ትክክለኛ መረጃን መያዝ፣ በሁሉም የልማት መስኮች የተትረፈረፈ ምርት ማምረትና አመራሩ በራሱ ከልመና አስተሳሰብ መላቀቅ እንዳለበትም ገልጸዋል።

በተለይም በእርዳታ እና በአደጋዎች ስም ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን ለማሳካትና እጅ ለመጠምዘዝ የሚደረጉ ጥረቶችን ለመመከት የጋራ አቋምና ብርታት ወሳኝ እንደሆነም ነው በአፅንኦት የጠቀሱት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም