ዳያስፖራው ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ ለማጠናከር ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ ለማጠናከር ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2016(ኢዜአ)፦ ዳያስፖራው ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ ለማጠናከር ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ገለጸ፡፡
የግድቡ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ህብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በቦንድ ግዥ፣ በ8100 አጭር የጽሑፍ መልዕክት፣ በዲጂታል ገቢ ማሰባሰቢያ፣ በአካልና በተለያዩ አማራጮች የተጠናከረ ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመዋል።
በዚህም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ጽሕፈት ቤቱ በውጭና በሀገር ውስጥ ለግድቡ ግንባታ የሚደረገውን ተሳትፎ ለማጠናከር እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ጋር በመተባበር ዳያስፖራው ለግድቡ ግንባታ በቀላሉ ድጋፍ የሚያደርግበት መተግበሪያ ይፋ መሆኑን አስታውሰው፤ ይህም የዳያስፖራውን ተሳትፎ ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም መሰል ትብብሮችን በማጠናከር ዳያስፖራው ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን ተሳትፎ ለማሳደግ ይሰራል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በላይነሕ አቅናው በበኩላቸው፤ ዳያስፖራው ለሕዳሴው ግድብና ለሌሎች የልማት ስራዎች የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
ለግድቡ ግንባታ ገንዘብ ከማዋጣት ባሻገር የማያቋርጥ እገዛ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በዚህም ባለፉት 13 ዓመታት ለግድቡ ግንባታ 50 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከዳያስፖራው መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ ደግሞ ይፋ በተደረገው መተግበሪያ አማካኝነት ዳያስፖራው ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
መተግበሪያው ይፋ በሆነበት በአንድ ሰዓት ውስጥ ብቻ ቃል የተገባውን ሳይጨምር 53 ሺህ የአሜሪካን ዶላር መሰብሰቡን ለአብነት በማንሳት፡፡