ቀጥታ፡

ፓኪስታን አዳዲስ የትብብር መስኮችን በመጨመር ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የማጠናከር ፍላጎት አላት - አምባሳደር ሚያን አቲፍ ሸሪፍ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2016(ኢዜአ)፦ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ማጠናከር የሚያስችሉ አዳዲስ የትብብር መስኮችን ለመጨመር እንደምትሰራ በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር ሚያን አቲፍ ሸሪፍ ገለጹ።   

የፓኪስታን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን በማውጣት ኢንቨስት እንዲያደርጉ እያበረታታች እንደምትገኝም አመልክተዋል።   

በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር ሚያን አቲፍ ሸሪፍ ረጅም ጊዜያትን ያስቆጠረው የሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና የትብብር አድማሱ እየሰፋ እንደሚገኝ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ሀገራቱ በተለያዩ መስኮች ግንኙነት እንዳላቸውና በባለ ብዝሃ ወገን የዲፕሎማሲ ትብብር አማራጭ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ላይ በጋራ እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል።

በአቪዬሽን ዘርፍ ያላቸው ግንኙነት እያደገ መምጣቱንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዓመት በፊት የፓኪስታን የንግድ ማዕከል ወደ ሆነችው ካራቺ የጀመረው የቀጥታ በረራ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

የተጀመረው በረራ ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ባሻገር ከአፍሪካ ጋር ያላትን ትብብር እንድታጠናክር መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በአዳዲስ የትብብር መስኮች መስራት የሚያስችላቸውን የተለያዩ ስምምነቶችን ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ፓኪስታን በኢትዮጵያ በትምህርትና በጤና ዘርፎች ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እንደምትፈልግ ገልጸው ሀገራቱ ግንኙነታቸውን ማጠናከር የሚችሉባቸው በርካታ አማራጮች እንዳሉም አንስተዋል።

ፓኪስታን ከአፍሪካ ጋር ባላት ግንኙነት ኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ መግቢያ በር ናት ብለዋል አምባሳደሩ።

በሌላ በኩል አምባሳደር ሚያን የኢትዮጵያ መንግስት በኢኮኖሚው ዘርፍ እያደረጋቸው የሚገኙ ማሻሻያዎችን አድንቀዋል።

በተለይም መንግስት ስር የነበሩ የኢኮኖሚ ተቋማት ወደ ግል ይዞታ እንዲዘዋወሩ የወሰደው እርምጃ መልካም የሚባል መሆኑን አመልክተዋል።

ፓኪስታን ከአውሮፓዊያን አቆጣጠር 1980ዎቹ አንስቶ በርካታ የመንግስት ተቋማትን ወደ ግል እንዲዛወሩ ማድረጓን ገልጸዋል።

የሁለቱ ሀገራት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ማዕቀፎች የኢንቨስትመንት ፍሰትን በመጨመር ግንኙነታቸውን ለማሳለጥ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ነው አምባሳደሩ የገለጹት።

ከዚህም አንጻር ፓኪስታን የሀገሪቷ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እያበረታታች እንደምትገኝም ጠቅሰዋል።  

ኢትዮጵያና ፓኪስታን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1973 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በቅርቡ የፓኪስታን የንግድ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ባደረገው ጉብኝት የፓኪስታን ሲያልኮት ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት አልባሳት በኢትዮጵያ ለማምረት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር መፈራረሙ የሚታወስ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም