በክልሉ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች እንደሚበረታቱ ርዕሰ መስተዳድር  አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ 

ሆሳዕና፤ ግንቦት 29 / 2016  (ኢዜአ) ፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል  በቴክኖሎጂ የታገዙ  አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን  ለማበረታታት ተገቢው  ድጋፍ እንደሚደረግ  የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።

ክልል አቀፍ የፈጠራ ስራዎች ውድድርና አውደ ርዕይ በሆሳዕና ከተማ በተከፈተበት ወቅት  አቶ እንዳሻው ጣሰው ፤ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚረዱ የፈጠራ ስራዎችን መደገፍ በክልሉ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት ፋይዳው የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።

የፈጠራ ስራን ማበረታታት ክልላዊ ለውጡን ከመደገፍ ባለፈ በውድ ዋጋ የሚገቡ ቴክኖሎጂዎችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካትና የውጪ ምንዛሪን ለማስቀረት የሚያግዝ እንደሆነም ተናግረዋል።

በክልሉ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን ለማፍለቅ የሚከናወኑ ተግባራትን የክልሉ መንግስት እንደሚያግዝም ገልጸዋል። 

የፈጠራ ስራዎችን አበልፅጎ መጠቀም ክልሉን በልማት ለማገዝና ተወዳዳሪ እንዲሆን እንደሚያስችለውም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

ለዚህም ስኬት  የክልሉ መንግስት የገንዘብ፣ የግብዓት፣ የክህሎት ስልጠናና ሌሎች ተግባራትን ድጋፍ  እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በክልሉ ፈጣን እድገት እንዲመዘገብ በፈጠራ ስራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ወጣቶችን ማበረታታትና ማብቃት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የክልሉ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በበኩላቸው ፤ በሳይንስና ፈጠራ የበቃ ትውልድ ለመፍጠር ቢሮው በልዩ ትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።በተለይም ከታች ጀምሮ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው እየበቁ እንዲሄዱ የመደገፍና ክትትል የማድረግ ስራም እንዲሁ።

ለዚህም ስኬት በክልሉ በሚገኙ ትምህርት ተቋማትና ኮሌጆች አማካኝነት የሚከናወኑ የምርምር ስራዎችን ለስኬት እንዲበቁ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ለፈጠራ ስራዎች መነሻ የሆነውን ሀሳብን በመደገፍ ለውጤት እንዲበቃ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል ያሉት ደግሞ የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ ናቸው።


 

በዘርፉ ዝንባሌ ያላቸውን ለማበረታታት በክልሉ በሚገኙ የትምህርት ተቋማት ለፈጠራ ስራ የሚሆኑ ግብዓቶችን የማሟላት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮና ትምህርት ቢሮ በትብብር ባዘጋጁት የሳይንስና የፈጠራ ስራዎች ውድድርና አውደ ርዕይ ላይ በመምህራን፣ ተማሪዎችና ኢንተርፕራይዞች የተዘጋጁ የፈጠራ ስራዎች ለዕይታ ቀርበዋል።

"በፈጠራ ስራ የዳበረ ትውልድ ለብልፅግና " በሚል መሪ ሀሳብ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚሁ መርሐ ግብር ላይ የክልሉ የአመራር አባላት፣  የፈጠራ ባለቤቶችና ተማሪዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም