ኢትዮጵያውያን በሕጋዊ የሥራ ሥምሪት በተለያዩ ሙያ ዘርፎች በሳዑዲ አረቢያ በስፋት ለማሰማራት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን በሕጋዊ የሥራ ሥምሪት በተለያዩ ሙያ ዘርፎች በሳዑዲ አረቢያ በስፋት ለማሰማራት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረዋል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያውያን በሕጋዊ የሥራ ሥምሪት በተለያዩ ሙያ ዘርፎች በሳዑዲ አረቢያ በስፋት ለማሰማራት የተጀመሩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሌንጮ ባቲ ተናገሩ።
አምባሳደር ሌንጮ ባቲ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና ሳዑዲ አረቢያ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ በሕዝብ ለሕዝብ፣ በባህል ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እየተሰራ ነው።
ይህንንም ተከትሎ 79 አባላት ያሉት የሳዑዲ አረቢያ የኢንቨስትመንትና የንግድ ልዑክ አዲስ አበባ መግባቱን ገልጸው በኢትዮጵያ ያለው ምቹ የኢንቨስትመንት አካባቢን በተመለከተ ገለጻ ተደርጎላቸዋል ብለዋል።
በተለይም መንግሥት ለኢንቨስትመንት ሥራ ምቹ መደላድል ለመፍጠር በፋይናንስና በሌሎች ዘርፎች ያደረጋቸውን ማሻሻያዎች በተመለከተም ገለጻ እንደተደረገላቸው አስረድተዋል።
የሳዑዲ ባለኃብቶችም በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው ይህንን እውን ለማድረግ ይሰራል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ከምትልካቸው ምርቶች ውስጥ ቡና፣ ሥጋ፣ ጥራጥሬ ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸው የንግድ ግንኙነቱን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በሕጋዊ የሥራ ሥምሪት በተለያየ የሙያ መስክ የሰለጠኑ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችም ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሄደው እንዲሰሩ የተጀመሩ የዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች መጠናከራቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የሳዑዲ አረቢያ አምባሳደር ፋድ ቢን ኡባይዱላይህ አልሁሜዳኒ (ዶ/ር) በበኩላቸው የኢትዮጵያና ሳዑዲ አረቢያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
የኢንቨስትመንት አማራጭ ለማየት ከፍተኛ አቅም ያላቸው ባለኃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይም የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።