የወጣቶችን የዲጂታል ስራ ፈጠራ ክህሎት በማጎልበት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው -በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2016(ኢዜአ)፦ የወጣቶችን የዲጂታል ስራ ፈጠራ ክህሎት በማጎልበት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)  ተናገሩ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ተግባራዊ የሚደረገውን አገር አቀፍ የክህሎት ስልጠና ፕሮግራም በይፋ አስጀምሯል።

 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ ፤ በአሁኑ ወቅት በሁሉም መስኮች ዲጂታል አሰራሮችን የመጠቀም ልምድ እየሰፋ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ 

ይህም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ከማድረግ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ ሚኒስቴሩ በተለይ የወጣቶችን የዲጂታል ስራ ፈጠራ ክህሎት ለማስፋት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ስለመሆኑ አንስተዋል።

ሚኒሰቴሩ ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያና ከጃፓኑ ዓለም አቀፍ ትብብር (JICA) ጋር የወጣቶችን የዲጂታል ስራ ፈጠራ ክህሎት ለማጎልበት የሚያስችል ስምምነት ማድረጉንም አስታውሰዋል፡፡

የስምምነቱ ዋነኛ ዓላማ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር በተለያዩ ዘርፎች የዲጂታል ክህሎት ስልጠናዎችን መስጠት መሆኑንም አክለዋል።

በዚህም በመጀመሪያው ዙር በተመረጡ ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች ለ10 ሺህ ዜጎች የዲጂታል ክህሎት ስልጠና ይሰጣል ብለዋል።

የክህሎት ስልጠናው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎችን ጨምሮ በአካባቢው ያሉና በተለያዩ የፈጠራ ስራ መሰማራት የሚፈልጉ ዜጎችንም ተደራሽ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ስልጠናውን ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የማስፋት ስራ እንደሚከናወን አረጋግጠዋል። 

የጃፓኑ ዓለም አቀፍ ትብብር(JICA) የኢትዮጵያ ተወካይ ቺ ሺሞንዲያራ በበኩላቸው ጃፓን በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን በመደገፍ አጋርነቷን እያሳየች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ውስጥ የቴክኖሎጂ እውቀት ሽግግርን የሚያጠናክሩ ስራዎች ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቁመው የጃፓኑ ዓለም አቀፍ ትብብር ለስልጠናው ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ተወካይ ማሳ ሚያሺታ ሳፋሪኮም ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በተደረገው ስምምነት መሰረት ለክህሎት ስልጠናው በቂ የኔትወርክ አቅርቦት ተደራሽ ይደረጋል ብለዋል።

ይህ የኔትወርክ አቅርቦት ከመጀመሪያው ዙር ጀምሮ ስልጠናው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ቀጣይነት እንደሚኖረውም አረጋግጠዋል።

በመጀመሪያው ዙር ባህርዳር፣ጂግጂጋ፣ድሬዳዋ፣ሃዋሳ፣መቀሌና አዳማ ዩኒቨርሲቲዎች የክህሎት ስልጠናው የሚጀመርባቸው መሆናቸው ታውቋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም