ቀጥታ፡

የቦረና ኔት ዎርክ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ እየተፋጠነ ነው - ዶክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ

ያቤሎ ፤ ግንቦት 29/2016(ኢዜአ)፦በተለያየ ምክንያት ከ10 ዓመት በላይ ግንባታው የተጓተተው የቦረና ኔት ዎርክ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እየተፋጠነ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ አስታወቁ።

በሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ የሚመራ የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች የቦረና ኔት ዎርክ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ሂደት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ሚኒስትሩ የግንባታ ሂደቱን ተመልክተው በሰጡት አስተያየት በቦረና ዞን በ'ሲአር ዋሽ" የሚሠራና በርካታ ወረዳዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የቦረና ኔት ዎርክ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ከ10 ዓመት በላይ በመጓተቱ ቅሬታ ሲቀርብ ቆይቷል።

ፕሮጀክቱ የዘገየው በግንባታ ቁሳቁሶች ጥራት ችግርና በዲዛይን ሥራዎች ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ በተደጋጋሚ በድርቅ እየተጎዱ ለሚገኙ የቦረና ህዝብና እንስሳት አገልግሎት እንዲሰጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ባደረጉት ምልከታም የውሃ ቦኖዎችና የእንስሳት ውሃ መጠጫ ስፍራዎች ውሃ የመያዝ አቅማቸው አስተማማኝ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ጠቅሰው፤ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ከስር ከስር አገልግሎት እየሰጠ እንድሄድ ይደረጋል ብለዋል።

ለግንባታው የፌደራል መንግሥት አንድ ቢሊየን ብር መድቦ እያስገነባ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ቀሪው ደግሞ በአፍሪካ ልማት ባንክ እና በኦሮሚያ ክልል መንግስት የሚሸፈን ይሆናል ብለዋል።

በአጠቃላይ 12 የጉድጓድ ውሃዎች ላይ ግንባታ እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን፤ አንድ ሺህ ሜትር ኪዩብ የሚይዙ አራት የውሃ ማጠራቀሚያዎች ግንባታም እየተጠናቀቀ ይገኛል ብለዋል።


 

የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አራርሳ አብዱለጢፍ በበኩላቸው 82 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍነው የቦረና ኔት ዎርክ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በ5 ክፍሎች የሚሰራ ነው ብለዋል።

የመጀመሪያው ዙር ሲጠናቀቅ በስድስት ወረዳዎች የሚገኙ በ66 ቀበሌዎችና 12 ከተሞች ለሚኖሩ 320 ሺህ ሰዎች እና 975 ሺህ 750 እንስሳት አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

በተለያየ ምክንያት ግንባታው በመዘግየቱ የህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን አንስተው አሁን ላይ በተቀናጀ መንገድ ግንባታው እየተፋጠነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

46 ቦኖዎችና 26 እንስሳት ማጠጫ ገንዳዎች የሚኖረው ፕሮጄክቱ በአሁኑ ሰዓት ግንባታቸውን ያጠናቀቁ አምስት ቦኖዎችን ጨምሮ የተወሰኑ የእንስሳት መጠጫ ገንዳዎች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናሉም ብለዋል።


 

በአከባቢያቸው የውሃ እጥረት በመኖሩ እንዲሁም በድርቅ ምክንያት በሰውና እንስሳት ላይ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል ያሉት ደግሞ በዞኑ የሃራዋዩ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ደንጌ ጢቃ ናቸው።

ተስፋ አድርገውት የነበረው ፕሮጄክቱ ግንባታ በመዘግየቱ ቅሬታ የነበራቸው ቢሆንም አሁን ላይ ግንባታው እየተፋጠነ በመሆኑ መደሰታቸውን አቶ ደንጌ ገልጸዋል።

በአፋጣኝ ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እንዲሰጥ የተጀመረው ጥረት መጠናከር እንዳለበትም ጠቁመዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም