የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከሲንጋፖር አቻቸው ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከሲንጋፖር አቻቸው ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2016(ኢዜአ)፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከሲንጋፖር አቻቸው ቪቪያን ብላከሪሽናን(ዶ/ር) ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
ውይይታቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው እንዲሁም የጋራ ትብብርን በሚጠይቁ አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
ውይይቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሀገሪቱ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የተከናወነ ሲሆን በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙትን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ተሰጥቶበታል።
ሁለቱ የስራ ሃላፊዎች በተለይ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም ቀጣይነት ያለው የልማት ትብብሮች ዙሪያ ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት አስታውቀዋል።
አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ሲንጋፖር በአለም አቀፍ ደረጃ የፋይናንስ፣ ዲጂታል ኢኮኖሚ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ማዕከል በመሆን ያላትን ስትራቴጂካዊ ስፍራ አድንቀዋል።
በዚህም የሲንጋፖር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ስማርት ከተማ ልማትና ስማርት ግብርናን በማስፋት፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ በቱሪዝም አገልግሎትና በትምህርት ዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።
የሲንጋፖር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪቪያን ብላክሪሽናን(ዶ/ር) በበኩላቸው ሲንጋፖር በአፍሪካ በተለይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማት ተሳትፎዋን ማጠናከር እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ ከባቢን ለመፍጠር እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ፊት ያለውን መልካም እድል ገልጸዋል።
የስራ ሃላፊዎቹ ከውይይቱ ባሻገር በሁለቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መካከል ቀጣይነት ያለው ውይይቶችና ትብብሮች እንዲኖር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርና በሲንጋፖር የትራንስፖርት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መካከል የዘርፉን ትብብር አስመልክቶ የፍላጎት ስምምነት ተፈርሟል።
ስምምነቱ በትራንስፖርት ዘርፉ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውንና የጋራ ተጠቃሚነትን ያሳድጋል ተብሏል።
አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ የሲንጋፖር ባለሀብቶች ኢትዮጵያን በመጎብኘት ያሉትን የኢንቨስትመንት አድሎች እንዲመለከቱ ግብዣ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።