ቀጥታ፡

የህብረት ስራ ማህበራት የአሰራር ችግሮችን በመፍታት ለውጤታማነት መስራት እንደሚገባቸው ተጠቆመ

ሐረር ፤ ግንቦት 29/2016 (ኢዜአ)፦  በሐረሪ ክልል የሚገኙ ህብረት ስራ ማህበራት  የአሰራር ችግሮቻቸውን በመፍታት ለውጤታማነት መስራት እንደሚገባቸው ተጠየቀ።

"ጊዜው የህብረት ስራ ነው" በሚል መሪ ሀሳብ  የህብረት ስራ ማህበራትን ለማጠናከር የተዘጋጀ ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው።

የክልሉ ህብረት ስራ ማህበራት ማደራጃና ማስፋፊያ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሚልኬሳ አህመድ እንዳሉት የህብረት ስራ ማህበራት በአገር በቀል ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ የጎላ አስተዋጽዎ ማበርከት ይችላሉ።

የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማጎልበት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ረገድ የህብረት ስራ ማህበራት ሚናቸውን እያበረከቱ መሆናቸውን ለአብነት አንስተዋል።

በክልሉ ከ29 ሺህ በላይ አባላትን የያዙ 451 የህብረት ስራ ማህበራትና ሁለት ዩኒየኖች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ እንደተናገሩት የህብረት ስራ ማህበራት ለአገራዊ እድገት ስኬት የጎላ ሚና ማበርከት ይችላሉ።

በተለይም የህብረት ስራ ማህበራት የሚስተዋልባቸውን የአሰራርና የአደረጃጀት ክፍተቶችን በመለየትና በመፍታት ለለውጥ ከሰሩ ያንን ሚናቸውን መወጣት ይችላሉ ብለዋል።

ማህበራቱ የአርሶ አደሩን ህይወት የሚቀይሩ ስራዎችን በማጠናከርም የዋጋ ንረትን የማረጋጋት ስራዎች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

መንግስትም የህብረት ስራ ማህበራቱን የመደገፍ እና የማጠናከር ስራውን አተኩሮ እንደሚሰራም ገልፀዋል።

የንቅናቄ መድረኩም በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመለየት መዘጋጀቱን በማከል።

በመድረኩ በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌቱ ወየሳ፣ የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ምክትል ኮምሽነር አቶ አብዲ ሙሐመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የህብረት ስራ ማህበራት ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም