ክልል አቀፍ የፈጠራ ስራዎች ውድድርና አውደ ርዕይ በሆሳዕና ከተማ ተከፈተ

ሆሳዕና ፤ግንቦት 29/2016 (ኢዜአ)፦ ክልል አቀፍ የፈጠራ ስራዎች ውድድርና አውደ ርዕይ "በፈጠራ ስራ የዳበረ ትውልድ ለብልፅግና " በሚል መሪ ሃሳብ በሆሳዕና ከተማ ተከፍቷል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው "በፈጠራ ስራ የዳበረ ትውልድ ለብልፅግና " በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀውን አውደ ርዕይ በይፋ ከፍተዋል።

አውደ ርዕዩ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ከሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በጥምረት ያዘጋጁት ሲሆን በትምህርት ተቋማትና በግል ኢንተርፕራይዞች የተሰሩ የፈጠራ ስራዎች ለዕይታ ቀርበዋል።

በክልሉ በሚገኙ የትምህርት ተቋማትና በግል ኢንተርፕራይዞች የተሰሩ ችግር ፈቺ  የፈጠራ ስራዎችን ማበረታታት፣ ማሳደግና እውቅና መስጠት የመድረኩ ዓላማ ስለመሆኑም ተገልጿል።

የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በእነዚህ ተቋማት ለማህበረሰብ ችግር  መፍትሄ የሚሆኑ የፈጠራ ስራዎች አሉ።

እነዚህን የፈጠራ ስራዎች አውደ ርዕይ በማዘጋጀት ለእይታ ክፍት ማድረግ ማህበረሰቡ የምርምር ስራዎችን ለመጠቀም እንዲነሳሳ ያስችለዋል ብለዋል ።

እንዲሁም ተተኪ የፈጠራ ስራ ባለቤቶችን ለመፍጠርና በዘርፉ ዝንባሌ ያላቸውን ዜጎች ለማበረታታት አጋዥ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

በመድረኩ በክልሉ በተለያየ የፈጠራ ስራ ላይ የተሰማሩ የፈጠራ ባለቤቶችን ውጤት ለውድድር በማቅረብ ለአሸናፊዎች ማበረታቻ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጀው የፈጠራ ስራዎች ውድድርና አውደ ርዕይ ክልሉን በመወከል የፈጠራ ስራ ውጤቶችን የሚያቀርቡ የፈጠራ ስራ ባለቤቶች እንደሚለዩም ገልጸዋል።

"በፈጠራ ስራ የዳበረ ትውልድ ለብልፅግና " በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው ክልል አቀፍ የፈጠራ ስራዎች ውድድርና አውደ ርዕይ ለሁለት ቀናት በተለያየ ኩነት ይካሄዳል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የፈጠራ ባለቤቶችና ተማሪዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም