ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዋን ዛሬ ታደርጋለች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2016 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ሶስተኛ የማጣሪያ ጨዋታውን ከጊኒ ቢሳው ጋር  ዛሬ ያከናውናል።

የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ 15 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው 'ስታዲዮ ናሲዮናል 24 ዲ ሴቴምብሮ" ሜዳ ላይ ይደረጋል።

በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ብሔራዊ ቡድን ለጨዋታው 33 ልዑካን አባላትን በመያዝ ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ወደ ስፍራው ማቅናቱ የሚታወስ ነው።

ቡድኑ ትናንትና ከትናንት በስቲያ ልምምዱን ያከናወነ ሲሆን የትናንት ልምምዱን ያደረገው ዛሬ ጨዋታው በሚካሄድበት ስታዲየም እንደሆነ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ከግብጽ፣ጊኒ ቢሳው፣ቡርኪናፋሶ፣ ሴራሊዮንና ጅቡቲ ጋር ተደልድሎ ጨዋታውን እያደረገ ይገኛል። 

ቡድኑ በምድቡ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች በአንዱ ተሸንፎ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቶ በ1 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

በማጣሪያ ጨዋታዎቹ በቡርኪናፋሶ 3 ለ 0 ሲሸነፍ ከሴራሊዮን ጋር ያለ ምንም አቻ ተለያይቷል። 

በ46 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ ሉዊስ ቦኣ ሞርቴ የሚመራው የጊኒ ቢሳው ብሔራዊ ቡድን በምድቡ 4 ነጥብ በመያዝ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ቦኦ ሞርቴ የጊኒ ቢሳው አሰልጣኝ ሆነው ከተሾሙ በኋላ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ዛሬ ከኢትዮጵያ ጋር ያደርጋሉ።

የቤኒኑ ጂንዶ ሉዊስ የሁለቱን አገራት ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመራሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አራተኛ የምድብ ጨዋታውን ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ሞሮኮ ላይ ከጅቡቲ ጋር ያከናውናል።


 

ምድብ አንድን ግብጽ በ6 ነጥብ እየመራች ሲሆን ቡርኪናፋሶ ጊኒ ቢሳውን በግብ ክፍያ በልጣ በ4 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ትናንት በዚሁ ምድብ በተደረገ ጨዋታ ሴራሊዮን ጅቡቲን 2 ለ 1 በማሸነፍ ነጥቧን ወደ 4 ከፍ አድርጋለች።

የምድቡ መሪ ግብጽ ከቡርኪናፋሶ ጋር ዛሬ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ 75 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው የካይሮ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ጨዋታዋን ታደርጋለች።

23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በአሜሪካ፣ሜክሲኮና ካናዳ ጣምራ አዘጋጅነት እ.አ.አ በ2026 የሚካሄድ ሲሆን በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 አገራት ይሳተፋሉ።

45 የአፍሪካ ሀገራት በዘጠኝ ምድብ ተከፍለው የዓለም ዋንጫ ጨዋታቸውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

አፍሪካ በዓለም ዋንጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 9 አገራት የምታሳትፍ ሲሆን በተጨማሪም በሌላ አህጉር ከሚገኝ አገር ጋር የጥሎ ማለፍ ጨዋታ አድርጎ ያሸነፈ አገር አህጉሪቷን ወክሎ የሚሳተፍ 10ኛ ቡድን ይሆናል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም