መንግስት ለስታርትአፕ የሰጠው ትኩረት እምቅ አቅማችንን አውጥተን ጥቅም ላይ እንድናውል በር ከፍቶልናል-የቴክኖሎጂ ስራ ፈጣሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለስታርትአፕ የሰጠው ትኩረት እምቅ አቅማችንን አውጥተን ጥቅም ላይ እንድናውል በር ከፍቶልናል-የቴክኖሎጂ ስራ ፈጣሪዎች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት ለስታርትአፕ የሰጠው ትኩረት እምቅ አቅማችንን አውጥተን ጥቅም ላይ እንድናውል በር ከፍቶልናል ሲሉ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ስራ ፈጣሪዎች ተናገሩ ፡፡
ስታርት አፖች በአንድ አገር የኢኮኖሚ ግንባታ ሒደት ውስጥ አይተኬ ሚና እንዳላቸው ይታወቃል።
ይህን መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየሰራ ይገኛል።
በተለይ የፈጠራ ባለቤቶች ችሎታቸውን በማውጣት ራሳቸውንና አገራቸውን እንዲጠቅሙ የሚያስችሉ የፋይናንስ ፣ የገበያ ትስስር፣ የሞራል እና መሰል ድጋፎችን አያደረገ ይገኛል።
የፈጠራ ባለሙያዎችም የተፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመስራት በአለምአቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ኢዜአ መንግስት የስታርት አፕ ምህዳሩን ምቹ በማድረግ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ተሰጥኦአቸውን በማውጣት ተጠቃሚ አንዲሆኑ እያበረከተላቸው ያለውን አስተዋጽኦ በተመለከተ ከስራ ፈጣሪዎች ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ወጣት ኤልያስ ታደሰ በዚሁ ወቅት፤ ሰዎች የጤና እክል ሲያጋጥማቸው በአቅራቢያቸው ያለን የጤና ተቋም የሚጠቁም "ብሉ ቴልዝ ኢትዮጵያ" የተባለ የሞባይል መተግበሪያ ማበልጸጉን ተናግሯል፡፡
መንግስት በዘረጋቸው የተለያዩ ድጋፎች በመታገዝ፤ ተሰጥኦውን በማውጣት ህልሙን ማሳካት መቻሉን ተናግሯል።
ረዥም የግብይት ሰንሰለትን በማሳጠር ህገ-ወጥ ደላሎችን ለመከላከል "አምራች ዶት ኮም" የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ ያበለጸገችው ደግሞ ወጣት ሜሮን ኤፍሬም ትባላለች፡፡
ወጣት ሜሮን ከአመታት በፊት ለዘርፉ ምንም አይነት ድጋፍ እንዳልነበር ጠቅሳ፤ አሁን ግን መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት ህልማችን እየኖርን እንገኛለን ነው ያለችው፡፡
ወጣት ተሾመ ረታ በተቋማት የሚወጡ የስራ ማስታወቂያዎች ከማንዋል ወደ ዲጅታል እንዲቀይሩ የሚያስችል "ሀርሜ ጆብስ" የተሰኘ መተግበሪያ ማበልጸጉን ገልጾ፤ በሂደቱ የመንግስት ድጋፍ እንዳልተለየው ገልጿል።
ሌላኛው ባለተሰጥኦ ወጣት ዮናታን አክሊሉ አርሶ አደሮች የዕለት ተዕለት የገበያ መረጃ የሚያገኙበት "አኪሎ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ" የተሰኘ ፕላት ፎርም ማዘጋጀቱን ተናግሯል።
በስራ ሒደቱ በመንግስት በኩል ለተደረገለት ድጋፍ እና ክትትል ምስጋና አቅርቧል፡፡
በቅርቡ የፈጠራ ባለሙያዎቹ የሚበረታቱበት የግሎባል ስታርትአፕ አዋርድስ አካል የሆነው ኢትዮጵያ ስታርትአፕ አዋርድስ መጀመሩ ይታወቃል።