የሳዑዲ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የሳዑዲ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2016(ኢዜአ)፦ የሳዑዲ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ በመጠቀም በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ።
በሳዑዲ አረቢያ የንግድ ምክር ቤት ፌዴሬሽን የተመራ ልዑካን ቡድን ትላንት ማምሻውን አዲስ አበባ መግባቱ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮ-ሳዑዲ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረሙ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን ለመፍጠር መንግሥት እያደረገ ያለውን የሪፎርም ሥራ አብራርተዋል።
በማብራሪያቸውም፤ መንግሥት የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት በቴሌኮም፣ በፋይናንስ፣ በሎጂስቲክስ፣ በንግድና በሌሎች ዘርፎች የውጭ ባለኃብቶች ገብተው እንዲሰሩ ክፍት መደረጉን አንስተዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት ከ80 በላይ የሕግና አስተዳደራዊ ሪፎርም በማድረግ ከ60 በላይ ዘርፎች ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለኃብቶች ለኢንቨስትመንት ክፍት መደረጉን ጠቁመዋል።
አሁን ላይ የአገር በቀል ምጣኔ ኃብት ማሻሻያ ምዕራፍ ሁለት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ የኢንቨስትመንት አካባቢን ምቹ ማድረግ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሃና አርዓያሥላሴ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ያለው የመሠረተ-ልማት አቅርቦት እንዲሁም አምራች የሰው ኃይል አገሪቱን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ አድርጓታል ብለዋል።
የገበያ አማራጮችና የሚሰጡ ማበረታቻዎችም ኢንቨስትመንት ለመሳብ ሌሎች አስቻይ ሁኔታዎች መሆናቸውንም አብራርተዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ፤ በኢትዮጵያ በፋይናንስ ዘርፉ እየተደረጉ ያሉ የፖሊሲ ለውጦች ለኢንቨስትመንት ዘርፍ እድገት ትልቅ አበርክቶ እንዳላቸው ገፀጸዋል።
የሳዑዲ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ በመጠቀም በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የልዑካን ቡድኑ መሪ እና የሳዑዲ ዓረቢያ የንግድ ምክር ቤት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሐሰን ሙጂብ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ እያደረጉ ያለው ጉብኝት የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማየት እድል የሚፈጠር መሆኑን ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ በግብርና ፣ በማምረቻው እና በምግብ ማቀነባበሪያ ዘርፎች ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ንግድና ዘፍፉ ማኅበራት ምክር ቤትና የሳዑዲ ዓረቢያ የንግድ ምክር ቤት ፌዴሬሽን አብረው መሥራት የሚያስችላቸውን ሥምምነት ተፈራርመዋል።