ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና የቻይና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር የሚያጎለብቱ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና የቻይና የባህል እንዲሁም የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር የሚያጎለብቱ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ገለጸ።

የቻይንኛ ቋንቋና ባህል በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲተዋወቅ አልሞ የሚካሄደው "ቻይኒዝ ብሪጅ" 23ኛው ዙር የኢትዮጵያ ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። 

በውድድሩ በኢትዮጵያ የቻይና ቋንቋን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሚያጠኑ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል። 

ቻይንኛን አንድ ክፍለ ጊዜ በሚወስዱ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች ጨምሮ በድምሩ 11 ተማሪዎች በውድድሩ ተሳትፈዋል።   

ተማሪዎቹ በቻይንኛ ቋንቋ ንግግሮች፣ የቻይንኛ ሙዚቃ፣ ስፖርት፣ የቻይና ባህል ላይ ያተኮሩ ጥያቄና መልስ እንዲሁም ሌሎች የመድረክ ሥራዎችን በማቅረብ ተወዳድረዋል።

በዚህም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቻይና ቋንቋ ተማሪዎች አብዱላፊዝ ከድር እና ዓለሙ ስዩም አሸናፊነት ተጠናቋል። 

አሸናፊዎቹም በቀጣይ በቻይና በሚካሄደው የ"ቻይኒዝ ብሪጅ" ዓለም አቀፍ የቋንቋ ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ ተገልጿል። 

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በበርካታ ዘርፍ እያደገ የመጣውን የኢትዮ-ቻይና ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ቋንቋ አስፈላጊ ነው። 


 

ኢትዮጵያውያን የቻይንኛ ቋንቋ ማወቃቸውም የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን ከማጠናከሩም በተጨማሪ  የሥራ አማራጮችን የሚያሰፋላቸው መሆኑን ገልፀዋል። 

ውድድሩ በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለውን የባህል ልውውጥና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክረውም ተናግረዋል።  

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ ሺን ኪንሚን በበኩላቸው፤ በቻይና የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን አስታውሰዋል። 


 

ይህም ለበርካታ ጊዜያት የቆየውን የኢትዮጵያና የቻይና ሕዝቦች ግንኙነት የበለጠ እያጠናከረው መምጣቱን ነው ያስረዱት።

23ኛው ዙር የቻይንኛ ቋንቋ ውድድርም ኢትዮጵያውያን የቻይናን ቋንቋና ባህል ለመረዳት የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያስችላል ብለዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም