የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ ዜጎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ ዜጎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2016(ኢዜአ)፦ በአገሪቱ የሚከናወነው የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ ዜጎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጠየቀ።
የዓለም የአካባቢ ቀን "የመሬት ማገገም፣ በረሃማነትና ድርቅን መቋቋም" በሚል መሪ ኃሳብ በፓናል ውይይት ተከብሯል።
በመድረኩ በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ የሚያተኩሩ የመወያያ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬነሽ መኩሪያ፤ የአየር ንብረት ለውጥ መዛባትን ለመከላከል የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ሊያጎለብቱ የሚችሉ ተግባራትን እንደ አገር ማከናወን አለብን ብለዋል።
መንግሥት በአገሪቱ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ባለፉት ዓመታት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን ተግባራዊ በማድረግ ዘርፈ-ብዙ ሥራዎችን በተከታታይ እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
እንዲያም ሆኖ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በተወሰኑ አካላቶች ብቻ ሊከናወን የሚችል አለመሆኑንም ገልጸው፤ ሕብረተሰቡን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅባቸውን አገራዊ ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በመዲናዋ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች በስፋት የተሰሩ ቢሆንም አሁንም ብዙ የቤት ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ከተማዋ የበርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን የምታስተናግድ ብሎም የዲፕሎማት መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን ለመኖር ምቹ መሆን አለባት ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ ከተማ አስተዳደሩ ለኅብረተሰቡ ምቹ ተፈጥሯዊ አካባቢን ለመፍጠር የኮሪደር ልማት ሥራን በማፋጠን ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌሎች የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችም ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰራባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የዓለም የአካባቢ ቀን በኢትዮጵያ ለ31ኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ51ኛ ጊዜ ነው ዘንድሮ የተከበረው።