ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባለፉት አስር ወራት ከ2 ሺ 700 ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ኃይል አመንጭቷል - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባለፉት አስር ወራት ከ2 ሺ 700 ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ኃይል አመንጭቷል
አዲስ አበባ፤ግንቦት 28/2016 (ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባለፉት አስር ወራት ከ2 ሺ 700 ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ኃይል ማመንጨቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታወቀ።
በሁለት ተርባይኖች ኃይል እያመነጨ የሚገኘው ግድቡ በ2016 በጀት ዓመት አስር ወራት ከዕቅዱ የ26 በመቶ ብልጫ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨቱን የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ ገልጿል።
በዘርፉ የዕቅድ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ጥሩወርቅ ሺፈራው እንደገለጹት ግድቡ በበጀት ዓመቱ አስር ወራት 2 ሺ 152 ነጥብ 8 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት አቅዶ 2 ሺ 711 ጊጋ ዋት ሰዓት አመንጭቷል።
ግድቡ የተሻለ ውሃ መያዙና ሁለቱ ተርባይኖች በሙሉ አቅማቸው ኃይል እንዲያመነጩ መደረጉ ለዕቅድ አፈፃፀሙ ከፍ ማለት ምክንያት እንደሆነም ሥራ አስኪያጇ አስታውቀዋል።
ባለፋት አስር ወራት በአጠቃላይ ከመነጨው የ16 ሺ 900 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የ16 በመቶ ድርሻ አለው ብለዋል።
ኃይል በማመንጨት ላይ የሚገኙት የግድቡ ሁለቱ ተርባይኖች እያንዳንዳቸው 375 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው ሲሆን በግድቡ ላይ የሚተከሉት ቀሪ 11 ዩኒቶች ኃይል ማምረት ሲጀምሩ አሁን በሀገሪቱ ያለውን የማመንጨት አቅም በ83 በመቶ ያሳድገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የተገኘው መረጃ ያመለክታል።