ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር የ128 ሚሊየን ብር የድጋፍ ሥምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2016(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኩላሊት እጥበት አገልግሎትን ለማጠናከር የሚውሉ የ128 ሚሊየን ብር የድጋፍ ሥምምነት ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር ተፈራረመ። 

ሥምምነቱን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዮሐንስ ጫላ (ዶ/ር)፣ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የማኅበራዊ ኃላፊነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አምባሳደር አሊ ሱለይማን እና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰሎሞን ንጉሴ ፈርመውታል።

የድጋፍ ሥምምነቱ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለዳግማዊ ምኒልክ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል  ለሦስት ዓመት የኩላሊት እጥበት አገልግሎት የሚውሉ ማሽኖችና ግብዓቶችን ግዥ ለመፈፀም የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዮሐንስ ጫላ (ዶ/ር) ድጋፉ በሆስፒታሉ የሚሰጠውን የኩላሊት እጥበት አገልግሎት ለማጠናከር እንደሚያስችል ገልፀዋል። 

ሚድሮክ ከዚህ ቀደም ለሆስፒታሉ ለኩላሊት እጥበት 40 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ ተቋሙ የሚያደርገው ድጋፍ አርዓያ የሚሆን ነው ብለዋል። 

ሌሎችም ተቋማት ተመሳሳይ ድጋፍ በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የማኅበራዊ ኃላፊነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አምባሳደር አሊ ሱለይማን በበኩላቸው፤ ሚድሮክ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል። 

በተለይም መንግሥት የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል እያደረገ ባለው የልማት ሥራዎችና በሌሎች መሰል ማኅበራዊ አገልግሎቶች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በዛሬው ዕለትም ለኩላሊት ታካሚዎች የሕክምና አገልግሎት የሚውል 128 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፤ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም