በምስራቅ ወለጋ ዞን አስተማማኝ ሰላምን ለማረጋገጥ በህዝብና መንግሥት የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት አስመዝግበዋል-- የዞኑ አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ወለጋ ዞን አስተማማኝ ሰላምን ለማረጋገጥ በህዝብና መንግሥት የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት አስመዝግበዋል-- የዞኑ አስተዳደር
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2016(ኢዜአ)፦ በምስራቅ ወለጋ ዞን አስተማማኝ ሰላምን ለማረጋገጥ በህዝብና መንግሥት የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገባቸውን የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደር ገለፀ።
የወለጋ ዞኖች ነዋሪዎች የለውጡን መንግሥት ለመደገፍ ያለመ ሰልፍ በነቀምቴ ባካሄዱበት ወቅት ሰላማቸውን ለመጠበቅ፣ ልማታቸውን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም ለውጡን ለማጽናትና ወለጋን የሰላምና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ እንደሚሰሩ መግለጻቸው ይታወሳል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት ሕዝቡ በሰላም፣ በአንድነትና በልማት ላይ በማተኮር እጅ ለእጅ ተያይዞ መሥራት እንዳለበት ጥሪ ማቅረባቸው አይዘነጋም።
ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲጸና መስራት እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የአካባቢው ሕዝብ በድጋፍ ሰልፉ ላይ በገባው ቃል መሰረት ከመንግሥት ጎን በመቆም ሰላም ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት በመሥራቱ ሰላም እየተረጋገጠ ይገኛል።
የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዋቅጋሪ ነገራ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በመቆም ለአካባቢው ሰላም መስፈን ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡
በተለይ እኩይ ዓላማ ያላቸውን አካላት በማጋለጥ ለተገኘው ሰላም ትልቅ ሚና መጫወቱን ነው የገለጹት፡፡
አሁን ላይ በዞኑ አስተማማኝ ሰላም በመስፈኑ ምክንያት ኢንቨስትመንት ማነቃቃትን ጨምሮ የልማት ፕሮጀክቶችን ዳግም ማስጀመር መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በዞኑ የሰፈነውን ሰላም በማስጠበቅ ረገድም መንግስት ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የምስራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ገመዳ ተፈራ በበኩላቸው በዞኑ አስተማማኝ ሰላም በመረጋገጡ ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው የእርሻ ስራዎቻቸውን እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መንግስት በምስራቅ ወለጋ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ግንባታ እያከናወነ ሲሆን ከዚህም ውስጥ የነቀምቴ- ቡሬ አስፋልት መንገድ ግንባታ መጀመር እንዲሁም የነቀምቴ አየር ማረፊያ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ተጠቃሽ ናቸው።