ቀጥታ፡

በአካባቢያቸው በስፋት እየቀረበ ያለው የአትክልት ምርት ገበያው እየተረጋጋ እንዲመጣ ማስቻሉን በባህርዳርና ደሴ ሸማቾች ገለጹ

ባህር ዳር፣ ግንቦት፤ 28 / 2016 (ኢዜአ)፡- በአካባቢያቸው በስፋት እየቀረበ የሚገኘው የአትክልት ምርት ገበያውን እያረጋጋ  መሆኑን በባህር ዳርና ደሴ ከተሞች አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ሸማቾች ገለጹ። 

የክልሉ ግብርና ቢሮ በበኩሉ በአማራ ክልል በዘንድሮ የበጋ መስኖ በስንዴና አትክልት ከለማው መሬት እስካሁን  29 ሚሊዬን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን አስታውቋል።

ከባህር ዳር ከተማ ሸማቾች  መካከል ወይዘሮ ሰርካለም እንየው እንዳሉት፤ ቀደም ሲል የአትክልት ዋጋ አሻቅቦ ነበር።  

በአካባቢያቸው በበጋ መስኖ የለማው የአትክልት ምርት ከየካቲት ወር መጨረሻ ጀምሮ ወደ ገበያ መግባት በመቻሉ 120 ብር ድረስ ይሸጥ የነበረው የአንድ ኪሎ ሽንኩርት ዋጋ ወደ 40 ብር፣ ቲማቲም ከ65 ወደ 25 ብር ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል።


 

ሌላኛዋ የባህር ዳር ከተማ ሸማች ወይዘሮ ልቅና ዘውዱ፤ የአትክልት ምርት ዋጋ በመቀነሱ በአቅማችን ልክ ገዝተን እንድንጠቀም አስችሎናል ሲሉ ተናግረዋል። 

በመስኖ የለማው የአትክልት ምርት በስፋት ወደ ገበያ መቅረቡ ዋጋው እንዲቀንስና ገበያው እንዲረጋጋ ዕድል ፈጥሯል ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ የደሴ ከተማ ሸማች ወይዘሮ መሰረት አሊ ናቸው፡፡

ቀደም ሲል በአካባቢያቸው የአንድ ኪሎ ሽንኩርት ዋጋ እስከ 145 ብር ደርሶ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ዋጋው በኪሎ  ከ35 ብር አንስቶ  እየተሸጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቲማቲም፣ ድንችና ሌሎች የአትክልት ምርቶች ዋጋም በግማሽ በመቀነሱ ገበያው እንዲረጋጋ አስተዋፅኦ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡


 

በክልሉ ግብርና ቢሮ የአትክልትና መስኖ ውሃ አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ይበልጣል ወንድምነው በበኩላቸው፤ በበጋ መስኖ ከ297 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአንደኛና ሁለተኛ ዙር ማልማት መቻሉን ገልጸዋል።

በአንደኛ ዙር መስኖ በስንዴ፣ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ጥቅል ጎመን፣ ቲማቲም ቃሪያና ሌሎች ከለማው መሬት እስካሁን 29 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

ከተሰበሰበው ምርት 25 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታሉ አትክልት ፤ ቀሪው የስንዴ ምርት መሆኑን አብራርተዋል።

በተለይ አትክልትን በክላስተር እና የዘር ጊዜን አራርቆ በመስኖ በማልማት እየተሰበሰበ ያለው ምርት የአቅርቦት ክፍተቱን በመሙላት የገበያ ዋጋ እንዲረጋጋ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።

በአንደኛና ሁለተኛ ዙር መስኖ የለማው ሙሉ በሙሉ ሲሰበሰብም 40 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሰው፤ ይህም ገበያው ይበልጥ የተረጋጋ እንዲሆን እንደሚያስችል አስረድተዋል።

በመጪው የክረምት ወቅትም ከ5 ሚሊዬን ኩንታል በላይ ሽንኩርት  ለማምረትም ከወዲሁ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት በመስኖ ከለማው 280 ሺህ ሄክታር መሬት 33 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም