ሰራዊቱ ከህዝቡ የወረሰው የጀግንነት ሥነ ልቦና በግዳጆች ሁሉ ውጤታማ አፈፃፀም እንዲኖረው አስችሎታል-ሜጀር ጀነራል ተስፋዬ አያሌው - ኢዜአ አማርኛ
ሰራዊቱ ከህዝቡ የወረሰው የጀግንነት ሥነ ልቦና በግዳጆች ሁሉ ውጤታማ አፈፃፀም እንዲኖረው አስችሎታል-ሜጀር ጀነራል ተስፋዬ አያሌው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2016(ኢዜአ)፦ መከላከያ ሰራዊት ከህዝቡ የወረሰው የጀግንነት ሥነ ልቦና በተሰማራባቸው ግዳጆች ሁሉ ውጤታማ አፈፃፀም እንዲኖረው አስችሎታል ሲሉ በመከላከያ ህብረት ዘመቻ ዋና መመሪያ የኃይል ሥምሪትና ክትትል መምሪያ ኃላፊ ሜጀር ጀነራል ተስፋዬ አያሌው ገለጹ፡፡
አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ውጤታማ ሪፎርም ከተተገበረባቸው የጸጥታና ደህንነት ተቋማት መካከል የመከላከያ ሰራዊት አንዱ ነው፡፡
በሪፎርሙ ኢትዮጵያን የሚመስልና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አስተማማኝ ዘብ የሆነ የመከላከያ ሰራዊት ተገንብቷል፡፡
በመከላከያ ህብረት ዘመቻ ዋና መመሪያ የኃይል ሥምሪትና ክትትል መምሪያ ኃላፊ ሜጀር ጀነራል ተስፋዬ አያሌው ለኢዜአ እንዳሉት፤ የመከላከያ ሰራዊት ጀግንነት የሚለካው በኢትዮጵያ ህዝብ ጀግንነት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ የሀገሩን ዳር ድንበር በማስጠበቅና ብሔራዊ ጥቅሙን በማስከበር ሂደት ልዩነቱን ወደ ጎን በመተው በአንድነት የሚዘምት ጠንካራ ሥነ ልቦና የተላበሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን የውጭ ወረራ ሲያጋጥማቸው የፖለቲካ ልዩነታቸው ሳይበግራቸው በጋራ እንደሚሰለፉ ዓለም የሚያውቀው ሀቅ ነው ብለዋል፡፡
ለአብነት በአድዋ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ አርበኞች ያለ ልዩነት በጋራ በመቆም የፋሽስት ጣሊያን ሰራዊትን በተባበረ ክንድ ማሸነፍ መቻላቸውን አንስተዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊት ከዚህ ጀግና ህዝብ የወጣ በመሆኑ ጠንካራ ሥነ ልቦና የተላበሰ፤ በአቋሙ የጸና የተሰጠውን ግዳጅ በብቃት መፈጸም የሚያስችል ቁመና ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሜጀር ጀነራል ተስፋዬ አያሌው በመከላከያ ሰራዊት ከተዋጊነት እስከ አዋጊነት በዘለቀው የ30 ዓመት የአገልግሎት ዘመናቸው ያገኙትን ልምድ "የጀግንነት ሥነ-ልቦና" በሚል ርዕስ በመጽሐፍ መልክ መሰነዳቸውንም ተናግረዋል፡፡
መጽሐፉ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ብቻ ሳይሆን መላ ኢትዮጵያውያን በማንበብ በተለይም ወጣቶች ወደ ጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ከመግባታቸው በፊት ለሀገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚከፈል መስዋዕትነት እስከምን እንደሆነ በቂ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች የሚገነቡት ኢትዮጵያዊ ሰራዊት መሆኑን የጠቆሙት ሜጀር ጀነራል ተስፋዬ፤ ህዝቡ የኢትዮጵያ ጠላቶች በሚያራግቡት የተሳሳተ መረጃ ሳይደናገር ደጀንነቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡