የጃንቹ ተራራ እና የሙዝ ደን

በቀደሰ ተክሌ ከሚዛን አማን ቅርንጫፍ

ከዓመት እስከ ዓመት የማይፋቅ ልምላሜ፤ ውብ ተፈጥሮ፣ ማራኪ መልክዓ ምድር እና ቸር አፈር ያለበት በመሆኑ የምድር ገነት የሚል ቅጽል ተሰጥቶታል- የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል። ተራራው ሳይቀር የሰጡትን ዘር የማብቀል ተፈጥሯዊ ግዴታን ተቀብሎ የሚወጣበት ሁኔታ አግራሞትን የሚጭር ነው።

የክልሉ ልምላሜ ምስጢር የጥብቅ ደኖች መብዛት ብቻ ሳይሆን የፍራፍሬ ተክሎችም ናቸው። አረንጓዴ ካባ የደረበው ክልሉ ከተፈጥሮ ሚዛን ጥበቃ የተሻገረ ሀብት ለማፍራት የሚያስችል ፀጋዎችን በጉያው ይዟል።

ለዚህ ደግሞ በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ ዞኖች መካከል በግብርና ምርቶች ራሱን ያስጌጠው የቤንች ሸኮ ዞን ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው። በዞኑ ደምቆ የሚታየው የደን ልምላሜ ዛፍ ብቻ ሳይሆን ምግብም ጭምር ነው። የማንጎ፣ የአቡካዶ እና የፓፓያ ዛፍ የሌለበት መስክ የለም። የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ የሆነው ሙዝ ደግሞ ከከተማ እስከ ገጠር የመኖሪያ ቤቶች ጥላና ግርማ ሞገስ ሆኖ ይታያል።

በቤንች ሸኮ ዞን ካሉ ወረዳዎች መካከል የደቡብ ቤንች ወረዳ አንዱ ነው። በዚህ ወረዳ ከሰብል ባሻገር የፍራፍሬ እና ቅመማ ቅመም ምርት እንደ ልብ ይመረታል። ከክልሉ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለሚወጣው የሙዝ ምርት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። የጃንቹ ቀበሌ ደግሞ ሰፊ የሙዝ ክላስተር ነው። 

በዚህ አካባቢ ተፈጥሮ እንኳ ከሕጉ ፈቀቅ ብሎ ለአካባቢው ፍራፍሬ እጁን ሰጥቷል። የተንጣለለው ተራራ ላይ ያለው አፈር ሙዝ እንደልቡ በቅሎ የሚያድግበት ሆኗል። በሌላኛው ተራራ ጫፍ ላይ ሆኖ ሲያዩት የጥብቅ ደን መልክ ይዟል።

የጃንቹ ተራሮች ለእርሻ የተጠመደ በሬን "አናስተናግድም" ቢሉ እንኳ በቀን በ60 ተሽከርካሪዎች ተጭኖ የሚወጣ ሙዝ ከመስጠት አልቦዘኑም። ክረምት ከበጋ የሚዘንበው ዝናብ እያጠበ የሚሸረሽረው አፈር እረፍት አግኝቶ ለአርሶ አደሮች ምንዳ እያበረከተ ነው።

አርሶ አደር መሠረት ገጂ የጃንቹ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፤ እርሳቸው ከስድስት ሄክታር የሚበልጥ የሙዝ ማሳ አላቸው። አቶ መሠረት እንደሚሉት፤ የሙዝ ምርቱ እጅግ ውጤታማና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ ነው። ብርቱው አርሶ አደር በዓመት ከ500 ሺህ ብር በላይ ገቢ ያገኛሉ።

የሙዝ ልማት የጀመሩበትን አጋጣሚ ሲያታውሱ ዛሬ በ250 ብር የሚሸጠውን አንድ የሙዝ ግንድ ያኔ በአንድ ብር ይሸጥ ነበር። እርሳቸውም 40 ግንድ በ40 ብር የሸጡላቸውን አርሶ አደሮች በአርዓያነት መከተላቸውን ያስታውሳሉ። ይህ ከ10 ዓመታት በፊት የተመለከቱት ተግባር የአካባቢው አርሶ አደሮች አጋጣሚውን ወደ መልካም ተሞክሮ በመቀየር በየጓሯቸው ሙዝ መትከል ጀመሩ፤ "እኔም እነሆ በየዓመቱ ማሳያን እየጨመርኩ ከባዶ ተነስቼ የስድስት ሄክታር ሙዝ ባለቤት የመሆን ደረጃ ላይ በቅቻለሁ" ሲሉ ገልጸዋል። 

"የተፋሰስ ልማት ዘመቻ ሙዝ በአካባቢው እንዲስፋፋ አድርጓል" ይላሉ፤ መሬት እንዳይሸረሸር ዳገታማ በሆኑ ቦታዎች ላይ ሙዝ እንዲተከል የግብርና ባለሙያዎች ማስተማራቸውን ይገልፃሉ፤ ዛሬ በዚህ ልክ ተራራው ሁሉ ጾም ከማደር ተላቆ የገንዘብ ምንጭ ሆኗል።

የጃንቹን የሙዝ ሀብት ከሚያጣጥሙ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ማላ ሻንቆ አንዱ ናቸው፤ በሁለት ሄክታር ማሳቸው ላይ ያለሙት ሙዝ የገቢ ምንጭ ሆኗቸዋል፤ በአዳዲስ ማሳ ላይ ተጨማሪ የሙዝ ችግኝ በመትከል ተክሉን እያስፋፉ ናቸው።

ማሳቸው ለእርሻ ሥራ የማይመች በመሆኑ ወደ ሙዝ ቀይረውታል፤ ይህም ሰብል አልምተው ከሚያገኙት የተሻለ ገቢ በማግኘት ቤተሰባቸውን እንደሚያስተዳድሩ ነው የሚናገሩት፤ ቀደም ሲል በአካባቢው ሙዝ የሚመረተው ለምግብነት ብቻ አልያም በአካባቢ ገበያ ላይ አብስሎ ለማቅረብ እንጂ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማስጫን አልነበረም።

የሙዝ ማሳቸውን እያሰፉ በመሄድ ለነጋዴ ከማስረከብ ተሻግረው በራሳቸው ለመላክ የሚያስችል ደረጃ ላይ የመድረስ እቅድ ይዘው እንደሚሠሩ ነው አቶ ማላ የተናገሩት።

የደቡብ ቤንች ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ባለሙያ አቶ ሳሙኤል ባካሽ እንደሚሉት፤ በአካባቢው ኩታገጠም የማምረት ዘዴን በመጠቀም የሙዝ ልማት እየተከናወነ ነው፤ የሙዝ ችግኝ ተከላ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ታቅፎ በዘመቻ ይተከላል።

በጃንቹ የሙዝ ክላስተር አራት ቀበሌዎች በኩታ ገጠም ሙዝ እያለሙ ነው፤ በዚህ የሙዝ ክላስተር የጃንቹ ተራራን ይዞ ከ2 ሺህ 500 በላይ ሄክታር ማሳ በሙዝ ተሸፍኗል፤ የሙዝ ማሳው ምርት መስጠት የጀመረ ሲሆን፤ አንዱ የአረንጓዴ አሻራ ቱሩፋት መሆኑን ነው አፅንኦት የሰጡት።

ለአካባቢው አየር ንብረት ተስማሚና ምርታማ የሙዝ ዝርያዎች እንዲተከሉ ሙያዊ እገዛ ይደረጋል፤ በተለይ ተፈጥሯዊ ልዩ ጣዕም ያለውን የሙዝ ምርት በልዩነት አምርቶ ለውጭ ገበያ የማቅረብ እቅድ ተይዞ የማስፋፋት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ነው።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልዱ በጪ እንዳሉት፤ በወረዳው ከ11 ሺህ ሄክታር በላይ የሙዝ ማሳ  ይገኛል፤ በቀን በአማካይ 60 የጭነት ተሽከርካሪዎች ያህል የሙዝ ምርት ወደ ማዕከላዊ ገበያ ይላካል፤ የሙዝ ማሳና ምርት መስፋፋት የወረዳው ሕዝብ የመንግስትን የልማት አቅጣጫ ተቀብሎ የመተግበር ልምድ ያዳበረ ለመሆኑ ማሳያ ነው። 

የቤንች ሸኮ ዞን በሁሉም ወረዳዎቹ ተመሳሳይ ምርት የሚመረትበት ነው። ይህ የሙዝ ምርት የሚዛን አማን ከተማን ጨምሮ በሌሎች ወረዳዎችም ይመረታል። የምርቱ መጨመር የአካባቢ የሙዝ ገበያን አረጋግቷል። ለአብነትም በሚዛን አማን ከተማ አራቱ በ20 ብር ሲሸጥ የነበረ የበሰለ ሙዝ አሁን በግማሽ ቀንሶ በ10 ብር እየተሸጠ ነው። 

የዞኑ ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ እና ኅብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ጉብላ እንደሚሉት፤ በዞኑ ከአምስት ዓመት በፊት 29 ሺህ ሄክታር የነበረው የፍራፍሬ ማሳ ዛሬ 84 ሺህ ሄክታር ደርሷል፤ከዚህም ውስጥ 44 ሺህ ሄክታር ማሳን የሸፈነው ሙዝ ነው። 

አሁን የተተከለው የሙዝ ችግኝ ሙሉ በሙሉ ምርት መስጠት ሲጀምር የምርት ማቅረብ አቅሙ ከፍ ይላል፤ ሙዙ በተፈጥሮ አፈር ላይ የሚበቅል እና የውጭ ንግድ ደረጃን የሚመጥን ተፈጥሯዊ ልዩ ጣዕም ያለው ምርት ነው።  

በሌላ በኩል የሙዝ ምርቱ ረጅም ኪሎ ሜትር ሳይጓዝ በቅርበት እሴት ታክሎበት ለገበያ የሚቀርብበትን ዕድል ለመፍጠር በቀጣይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ርብርብ እንደሚደረግ ነው የሚናገሩት፤አምሯቹ አርሶ አደር ተገቢውን ዋጋ ከምርቱ አግኝቶ ተጠቃሚነቱን እንዲያሳድግ 'የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ በአካባቢው ያስፈልጋል' የሚል እምነት አላቸው።

ሙዝ ለቤንች ሸኮ እና አካባቢው ጥላ ነው፤  ምርቱ ምግብ ነው፤ ከምሽት ገበያ እስከ ማዕከላዊ ገበያ ተጭኖ በመሸጥ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ሀብት ነው፤  ስለዚህ በጅምር ሥራዎች የታየው ለውጥ አድጎ ከፍ እንዲል ለአርሶ አደሩ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ተገቢ ነው።

የአንድ አካባቢ ልማትና ዕድገት የአካባቢ የተፈጥሮ ፀጋን መሠረት ያደርጋል፤ የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ ለይቶ ተስማሚ የልማት ሥራዎችን ማስፋፋት ከተቻለ የሚፈልገውን ለውጥ የማያመጣበት ምክንያት አይኖርም፤ በሌላ በኩል ለአንድ ምርት የማይሆነውን አካባቢ "አይሆንም በቃ"ብሎ እጅ እግር አጣጥፎ ከመቀመጥ ይልቅ የሚሆነውን አጥንቶ መተካትን ከጃንቹ አርሶ አደሮች የተራራው ሙዝ ልማት መማር ይቻላል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም