በምስራቅ ወለጋ ዞን 13 መካከለኛና አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ወለጋ ዞን 13 መካከለኛና አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው
ምስራቅ ወለጋ፤ ግንቦት 28/2016(ኢዜአ)፦ በምስራቅ ወለጋ ዞን ከ805 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ 13 መካከለኛና አነስተኛ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን የዞኑ የመስኖ ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ።
በፌዴራል መንግስት ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ደግሞ በአንገር ወንዝ ላይ ትልቅ የመስኖ ግድብ ለመገንባት ከተቋራጩ ጋር ውል ተገብቶ ወደ ግንባታ ሂደት እያመራ መሆኑም ተጠቁሟል።
የምስራቅ ወለጋ ዞን መስኖ ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መንግሥቱ አለማየሁ ለኢዜአ እንደገለፁት፥ እንደ ሀገር የመስኖ ግብርናን ለማፋጠን የሚያስችል መሰረተ ልማት ግንባታ በዞኑ እየተከናወነ ነው።
ለዚህም በክልሉ፣ በዞን እና በወረዳ በጀት የተለያዩ የመስኖ ግድብ ግንባታዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በዚህም ከ805 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ 13 መካከለኛና አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ በፍጥነት እየተከናወኑ ሲሆን ግንባታቸው ሲጠናቀቅ ከ3 ሺህ 400 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ብለዋል።
እየተገነቡ ካሉት ፕሮጀክቶች መካከልም አራቱ በዚህ ዓመት ተጠናቀው አገልግሎት እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል።
በዞኑ በአንገር ወንዝ ላይ የፌዴራል መንግስት ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባው ትልቅ የመስኖ ፕሮጀክት ውል እንደተገባለትም ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የግንባታ ሂደቱን ለመጀመር መሳሪያዎችንና ባለሙያዎችን በማስገባት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፥
ግንባታው በሁለት ዓመታት ሲጠናቀቅ በአካባቢው በሚገኙ ሁለት ዞኖች የሶስት ወረዳ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያርግ ተናግረዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የምስራቅ ወለጋ ዞን አርሶ አደሮች በመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ መፋጠን መደሰታቸውን ገልጸው፥ ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ የበጋ ልማትን እንዲያከናውኑ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው አንስተዋል።
በመሆኑም የመስኖ ግድቦቹ ግንባታ እስከሚጠናቀቁ የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
መንግስት በምስራቅ ወለጋ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ግንባታ እያከናወነ ሲሆን ከነቀምቴ- ቡሬ የሚወስደው የአስፋልት መንገድ ግንባታ እንዲሁም የነቀምቴ አየር ማረፊያ ግንባታ ተጠቃሽ ናቸው።