በአዲስ አበባ የተካሄደው የአጀንዳ ልየታ ምክክር ምዕራፍ ኢትዮጵያውያን ለችግሮቻቸው የጋራ መፍትሄ ለማበጀት ቁርጠኝነታቸውን ያሳዩበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የተካሄደው የአጀንዳ ልየታ ምክክር ምዕራፍ ኢትዮጵያውያን ለችግሮቻቸው የጋራ መፍትሄ ለማበጀት ቁርጠኝነታቸውን ያሳዩበት ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2016(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአጀንዳ ልየታ ምክክር ምዕራፍ ኢትዮጵያውያን ለችግሮቻቸው የጋራ መፍትሄ ለማበጀት ቁርጠኝነታቸውን ያሳዩበት መሆኑን የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የአዲስ አበባ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ መጠናቀቅን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፥ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተወካዮች በአምስት ቡድኖች ተከፍለው አጀንዳዎቻቸውን በማሰባሰብ ለኮሚሽኑ ማስረከባቸውን ተናግረዋል፡፡
መድረኩ ያለምንም ገደብ በነጻነት ተከናውኖ በተሳካ መልኩ መጠናቀቁንም ነው የገለጹት፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች አጀንዳዎቻቸውን በማቅረብ ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውንም ዋና ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ የተካሄደው የምክክር ምዕራፍ የአጀንዳ ልየታ ሂደት ኢትዮጵያውያን ለችግሮቻቸው የጋራ መፍትሄ ለማበጀት ቁርጠኝነታቸውን ያሳዩበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ተሳታፊዎች የወከሏቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችና ባለድርሻ አካላት ድምጽና ፍላጎት ለማሰማት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውንም አመላክተዋል።
አጀንዳዎቹ ሲጠቃለሉም ሀሳቦች እንዳይዋጡ ወይም ሳይካተቱ እንዳይቀሩ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ጠቁመዋል።
በሂደቱ የተለያየ አመለካከትና ሀሳብ ያላቸው ወገኖች በአንድ አዳራሽ ተሰባስበው በጠረጴዛ ዙሪያ ሀሳብ የተለዋወጡበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ይህም አለመግባባቶችና የሀሳብ ልዩነቶችን በመመካከር የመፍታት ባሕል ለማዳበር ለምናደርገው ጉዞ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ወስዶናል ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ በቀጣይም በምክክር ምዕራፍ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትን በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና በክልሎች እንዲሁም በፌደራል እና በዲያስፖራ ደረጃ እንደሚያከናውን አመላክተዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ በአዲስ አበባ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ እንዲሳካ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።