ቀጥታ፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የስራና ክህሎት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማትን ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2016(ኢዜአ)፦ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የስራና ክህሎት ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማትን የስራ እንቅስቃሴ ጎበኙ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ለፈጠራ ሀሳብና ለምርምር ምቹ የሆነ የስራ አካባቢ እንዲፈጠር ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት በኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የተከናወኑ የልማት ስራዎችና የኢኖቬሽን ውጤቶችንም ተመልክተዋል።


 

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል እንደገለጹት፤ በኢንስቲትዩቱ ለፈጠራ ሀሳብ ማፍለቂያ እና ለምርምር ምቹ ምህዳር ተፈጥሯል ።

ኢንስቲትዩቱ ከሀገር የልማት ግብ አኳያ ብቁ ሙያተኞችን እያሰለጠነ እንዲሁም በፈጠራና በእውቀት የሚመራ ኢኮኖሚ መገንባት የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመፍጠር ላይ ነው ብለዋል።

በየዓመቱ 10 ሺህ ተማሪዎችን እያሰለጠነ የሚገኘው የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩቱ፤ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂስቶች መፍለቂያ እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰዋል።


 

የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቱትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) በበኩላቸው የሀገርን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያሳካ ብቁ የሰው ኃይል ስልጠና እና ምርምር  ዋነኛ ትኩረታችን ነው ብለዋል።

በዚህም የኢትዮጵያን ግብርና፣ ጤና፣ ቱሪዝም፣ ግብርና፣ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ ኮንስትራክሽንና ሌሎችን ይበልጥ የሚያዘምኑ በርካታ ቴክኖሎጂ በኢንስቲትዩቱ መፈጠራቸውን አንስተዋል።

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም