በኢትዮጵያ የጨቅላ ሕጻናት የመስማት ችሎታ ምርመራ አገልግሎት ሊጀመር ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የጨቅላ ሕጻናት የመስማት ችሎታ ምርመራ አገልግሎት ሊጀመር ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የጨቅላ ሕጻናት የመስማት ችሎታ ምርመራ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መርሐ ግብር ይፋ ሆኗል።
የኦስትሪያ መንግስት ከጤና ሚኒስቴርና መስማት ለኢትዮጵያ ማህበር ጋር በመሆን መርሐ ግብሩን በአዲስ አበባ ይፋ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ዶክተር ሲሞን ናፕ የጤና አገልግሎትና የጤና እንክብካቤ ማግኘት ሰብዓዊ መብት እንደሆነና ዘርፉ ከዘላቂ ልማት ግቦች መካከል የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል።
የኦስትሪያ መንግስት የጤና አገልግሎትን ተደራሽነት በኢትዮጵያ ለማስፋት እየሰራ እንደሚገኝና የመስማት ችሎት ምርምራ ፕሮጀክት የዚሁ ስራ አካል መሆኑን አመልክተዋል።
በመርሐ ግብሩ አማካኝነት ኦስትሪያ በአገሪቷ የልማት ኤጀንሲ (ADA) በኩል አዲስ የተወለዱ ጨቅላ ሕጻናት የመስማት ችሎታ አገልግሎት ተፈጻሚነት ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል።
ድጋፉ በምርምራ አገልግሎቱ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይልና የአቅም ግንባታ እንዲሁም የምርምራ ቴክኖሎጂና ግብአቶችን ማሟላትን እንደሚያካትት ነው አምባሳደሯ የገለጹት።
የኦስትሪያው ዓለም አቀፍ ከመስማት ጋር የተያያዙ መሳሪያዎችንና ግብዓቶችን የሚያመርተው ዓለም አቀፍ የጤና ቴክኖሎጂ ኩባንያ ሜድ-ኤል (MED- EL) የግብዓት ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
በቀጣይም ኦስትሪያ የጨቅላ ሕጻናት የመስማት ችሎታ ምርመራ አገልግሎት እንዲስፋፋ ድጋፍ እንደምታደርግ ጠቅሰው ሁሉም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ለመርሐ ግብሩ ውጤታማነት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የጤና ሚኒስቴር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ፋጡማ ሰይድ በኢትዮጵያ የጨቅላ ሕጻናት የመስማት ችሎታ ምርመራ አገልግሎት አልነበረም ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት አዲስ የተወለዱ የጨቅላ ህጻናት የመስማት ምርመራ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ መሆኑን ጠቅሠው በኢትዮጵያ መርሐ ግብሩን ለማስጀመር ከአጋር አካላት ጋር ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ለዚህም በኦስትሪያ ከሚገኝ ሜድ-ኤል (MED- EL) የተሰኘ ኩባንያ በኦስትሪያ የልማት ትብብር ኤጄንሲ አማካኝነት የመስማት መጠን መመርመሪያ መሳሪያ ድጋፍ ማበርከቱን ጠቁመዋል።
በዚህም የመመርመሪያ መሣሪያ ድጋፍ አዲስ የተወለዱ ጨቅላ ህጻናትን የመስማት ችሎታ ምርመራ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በኮሪያ እና በምግባረ ሰናይ ጠቅላላ ሆስፒታል የሚጀመር መሆኑን ገልጸዋል።
ምርመራው በሆስፒታሎቹ ለሚገኙ ባለሙያዎች ስልጠና ከተሰጠ በኋላ በሳምንቱ መጨረሻ በአዲስ አበባ በተመረጡ አራት ሆስፒታሎች እንደሚጀመር ጠቁመዋል።
የመስማት ለኢትዮጵያ ማህበር ፕሬዝዳንትና ከአንገት በላይ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ኢስሐቅ በድሪ በበኩላቸው የመስማት ችግር የሚታይ ባለመሆኑ በርካታ ሕጻናት ችግሩ እንዳለባቸው በቤተሰቦቻቸው የሚታወቀው እድሜያቸው ከፍ ካለ በኋላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ሕጻናት ገና ሲወለዱ ለመስማት ችግር ተጋላጭ እንዳይሆኑ አስቀድሞ የምርምራና ሕክምና አገልግሎት ማግኘት እንደሚገባቸውና መርሐ ግብሩ በርካታ ሕጻናትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ለኢትዮጵያ የሕክምና ባለሙያዎች የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ እንደሚያስችልም አመልክተዋል።
በአዲስ አበባ ይፋ የሆነው የጨቅላ ሕጻናት የመስማት ችሎታ ምርመራ አገልግሎት በቀጣይ በሌሎች አካባቢዎችም እንደሚቀጥል ተገልጿል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ 32 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕጻናት የመስማት ችግር እንዳጋጠማቸው የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ከነዚህም ውስጥ ከ25 እስከ 80 በመቶው የሚገኙት ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ነው።
ሕጻናት ተወልደው አንድ ወር ሲሞላቸው የመስማት ችሎታ ምርመራ ማድረግ እንደሚኖርባቸው የሕክምና ባለሙያዎች የሚገልጹ ሲሆን ይህም ሕጻናቱን ከመስማት ችግር ለመከላከል ወሳኝ መሆኑን ይናገራሉ።
ኢትዮጵያና ኦስትሪያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1905 ሲሆን ኦስትሪያ የኢትዮጵያ ሁነኛ የልማት አጋር ሆናም ትጠቀሳለች።