ቀጥታ፡

ከደጋማ አካባቢዎች የሚገኘውን የቆዳ ምርት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ከከፍተኛ ወይም ከደጋማ አካባቢዎች የሚገኘውን ሀይላንድ ቆዳ  ምርት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና ባለድርሻ ተቋማት ጋር  በመተባበር በኢትዮጵያ የሀይላንድ ቆዳ ዙሪያ በሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ምክክር አድርጓል።

ኢትዮጵያ ጥራት ያለው የቆዳ ምርት ለዓለም ገበያ ከሚያቀርቡት ግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካና ሞሮኮ መካከል አንዷ ነች፡፡ 

የሀይላንድ ቆዳ በኢትዮጵያ በአብዛኛው በከፍተኛ ወይም ደጋማ አካባቢዎች ከሚገኙ በጎች በከፍተኛ ጥራት የሚመረት የቆዳ አይነት ነው፡፡ 

ይሄንን ከፍተኛ ጥራት፣ ልስላሴ እና ጥንካሬ ያለው የቆዳ ምርት በዓለም ገበያ በመለያ/ብራንድ ለማቅረብ እየሰራች ነው፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ስለሺ ለማ፤ የኢኮኖሚያዊ እድገት ከሚያረጋግጡ የማምረቻ ዘርፎች መካከል የቆዳ ምርት ዋነኛው መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኘው የሀይላንድ ቆዳ በጥራትና ጥንካሬው በዓለም ገበያ ተፈላጊ በመሆኑ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ይገባል ብለዋል፡፡

በመሆኑም እንደ ሀገር ያለውን የተፈጥሮ ጸጋ በአግባቡ በመጠቀም በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረውን አበርክቶ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቆዳ እና ሌጦ ውጤቶችን የጥራት ደረጃ የበለጠ ማሳደግ፣ ምርቱ በስፋት የሚመረትበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ከግብአት ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮችን መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡

በዚህም ሚኒስቴሩ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በቅርቡ የቆዳ ስትራቴጂ ተግባራዊ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ስትራቴጂው ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የዘርፉ ተዋናዮችም በኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ከፍተኛ ማሻሻል እያሳየ መሆኑን ጠቅሰው በችግሮች ለይ ተወያይቶ ዘላቂ መፍትሄ ማስቀመጥ ይገባል ብለዋል፡፡


 

ባህርዳር የሚገኘው የዴብ ኢምፔክስ የቆዳ ልማት ኢንተርፕራይዝ ምክትል ስራ አስኪያጅ ብሩክ ሀይሉ፤

ጥራቱን የጠበቀ ቆዳ ለማምረት የጋራ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም