ቀጥታ፡

"የጀግንነት ሥነ-ልቦና" መጽሐፍ ኢትዮጵያ የመጣችበትን፣ ያለችበትንና ሉአላዊነቷን ለማስከበር የሚያስፈልገውን የጀግንነት ሥነ-ልቦና የሚያስተምር ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2016(ኢዜአ)፦"የጀግንነት ሥነ-ልቦና" የተሰኘው የሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው የወታደራዊ ሥነ-ልቦና መጽሐፍ ኢትዮጵያ የመጣችበትን፣ ያለችበትን ደረጃና ሉአላዊነቷን ለማስከበር የሚያስፈልገውን የጀግንነት ሥነ-ልቦና የሚያስተምር መሆኑ ተገለጸ። 

በሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው የተጻፈው "የጀግንነት ሥነ-ልቦና" የወታደራዊ ሥነ-ልቦና መጽሐፍ በመጪው ዓርብ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ይመረቃል።

የመጽሐፉን ምርቃት በማስመልከት የተቋቋመው ኮሚቴ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው ከመሠረታዊ ወታደርነት እስከ ከፍተኛ ጄኔራል መኮንንነት በታማኝነትና ቅንነት በተለያዩ ኃላፊነቶች እያገለገሉ የሚገኙ ናቸው። 

ጄኔራል መኮንኑ በማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም የመጀመሪያ ዲግሪ፣ እንዲሁም በሊደርሺፕና መልካም አስተዳደር የሁለተኛ ዲግሪ አላቸው። 

በወታደራዊ ትምህርት ካዴት፣ ስታፍ ኮሌጅ፣ እንዲሁም በስዊድን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የወታደራዊ ስታፍን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ከፍተኛ የአመራር ኮርስ ወስደዋል። 

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዳርፉር ሰላም ማስከበር ሴክተር ሦስት የዘመቻ ኃላፊ፣ የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የዘመቻና የመረጃ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል።


 

በአጠቃላይ ለ30 ዓመታት በዘለቀው የወታደራዊ ኃላፊነታቸው ከተዋጊነት እስከ አዋጊነት በማገልገል በሰሜኑ ጦርነት በነበራቸው የጎላ አበርክቶ ምርጥ የዘመቻ መኮንን ሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በተጨማሪም በ30 ዓመት አገልግሎት ዘመናቸው የአምስት፣ አሥር፣ 15፣ 25 እና የ30 ዓመት አገልግሎት ሜዳሊያና ኒሻን ተሸላሚም ናቸው። 

በቅርቡ አልሸባብ ኢትዮጵያን ለማተራመስ በምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል ያደረገውን ሙከራ በመሪነት ማክሸፍ ችለዋል። 

ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው ከዚህ ቀደም "Leadership challenge managing the causes of conflict between Geri and borena" ጽፈዋል። 

"የጀግንነት ሥነ-ልቦና" መጽሐፍ ደራሲ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው ለ30 ዓመታት በዘለቀው የወታደራዊ አገልግሎታቸው ካካበቱት ልምድ ለኢትዮጵያውያን መማሪያ እንዲሆን ያዘጋጁት መሆኑን ገልፀዋል።

መጽሐፉ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ብቻ ሳይሆን መላ ኢትዮጵያውያን ቀድመው በማንበብ በቂ የሥነ- ልቦና ዝግጅት ማድረግ የሚችሉበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተለይም ወጣቶች ወደ ጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ከመግባታቸው በፊት ለሀገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚከፈል መስዋዕትነት እስከምን እንደሆነ በቂ ግንዛቤ ያገኙበታል ብለዋል፡፡

የኮሚቴው ሰብሳቢ ቦና ደበላ፤ በ11 ምዕራፎች እና በ 360 ገፆች የተቀነበበው የጀግንነት ሥነ-ልቦና መጽሐፍ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ ሶማሊኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች መዘጋጀቱ የተደራሽነቱን አድማስ ያሳያል ብለዋል። 


 

በተጨማሪም መጽሐፉ ሀገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በማንበብ የትናንት ጀግንነታቸውን የነገ ዝግጅታቸውን ስንቅ የሚይዙበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

መጽሐፉ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን በጀግንነት እንዴት እንዳመጧት፣ ምን ላይ እንዳለች እንዲሁም በቀጣይ ሉዓላዊነቷንና ዳር ድንበሯን ለማስከበር የሚያስፈልገውን የጀግንነት ሥነ-ልቦና ምን እንደሚመስል የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮሚቴው አባል ተስፋዬ ንዋይ በበኩላቸው፤ መጽሐፉ ከታሪካዊ ሥነ-ልቦና ዳሰሳ እስከ ንድፈ-ኃሳባዊ መርሆዎች የወታደራዊ ሥነ-ልቦናን አተገባበር የሚተነትን መሆኑን ገልፀዋል፡፡


 

በ11ዱ ምዕራፎች የወታደራዊ ሥነ-ልቦና ምንነት፣ ወታደራዊ ጀግንነት፣ ወታደራዊ ሳይንስ፣ የጦርነት ሥነ- ልቦና ዝግጅት፣ የወታደራዊ አመራር ጽንሰ-ኃሳብና የተግባር አመራር የቀረበበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ ከውጊያ በፊት፣ በውጊያ ወቅትና በኋላ ሊኖር የሚገባውን የጀግንነት ሥነ-ልቦና ዝግጅትና ወኔ በዝርዝር ያስረዳል ብለዋል፡፡

ከመጽሐፍ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ለእናት ሀገራቸው ዳር ድንበር መከበር አካላቸውን ላጡ ጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆች ድጋፍ የሚውል ይሆናል ተብሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም