የአዋጁ መሻሻል በፖለቲካ ምህዳሩ ሰላማዊ የትግል አማራጭን የሚያሰፋ ነው- የምክር ቤቱ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የአዋጁ መሻሻል በፖለቲካ ምህዳሩ ሰላማዊ የትግል አማራጭን የሚያሰፋ ነው- የምክር ቤቱ አባላት
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር ማሻሻያ አዋጅ በፖለቲካ ምህዳሩ ከትጥቅ ይልቅ ሰላማዊ የትግል አማራጭን የሚያሰፋ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክ ቤት አባላት ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 30ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር ማሻሻያ አዋጅን አፅድቋል።
በምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ የማሻሻያ አዋጁን አስፈላጊነት በተመለከተ ለምክር ቤት አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም የአዋጁ መሻሻል በትጥቅ ትግል ስልጣን መያዝ የሚፈልጉ ሃይሎች ህጋዊና ሰላማዊ አማራጭን እንዲከተሉ የሚያደረግ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሰላምን ለማፅናት የተጀመረውን ጥረት የሚያግዝ አስፈላጊ የሆነ ማሻሻያ የተደረገበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በሃይልና በጠመንጃ ችግሮችን ለመፍታት መሞከር ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ የለውጡ መንግስት ለሰላማዊ አማራጮች በትጋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የፖለቲካ ባህልን ለማሳደግ የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻልና በትጥቅ ትግል የሚሳተፋ ቡድኖች ወደ ህጋዊ መንገድ እንዲመጡ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርም አንዱ ትኩረት መሆኑን አንስተዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ የትጥቅ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር ማሻሻያ አዋጅ በፖለቲካ ምህዳሩ ከትጥቅ ይልቅ በሃሳብ የበላይነት ሰላማዊ የትግል አማራጭን የሚያሰፋ ነው ብለዋል።
የፍትህ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፤ የዓዋጁ መሻሻል ዋነኛ ዓላማ ምህረት መስጠት ይቅርታ ማድረግና ተጠያቂነትን ማስቀረት አይደለም ሲሉ አስረድተዋል።
በትጥቅ እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ አካላት የፈጸሙት ጉልህ የህግ ጥሰት በሽግግር ፍትህ ፖሊሲ በሚዘጋጁ የህግ ማዕቀፎች የሚታይ እንደሚሆንም አንስተዋል።
በመሆኑም የማሻሻያ አዋጁ በተለያዩ ክልሎች በትጥቅ ትግል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖችን ወደ ህጋዊ መንገድ የሚያመጣ ይሆናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር ማሻሻያ አዋጅ በምክር ቤት አባላት ውይይት ከተደረገበት በኋላ በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል፡፡