በሲዳማ ክልል ጽዱና ከብክለት ነጻ የሆነ አካባቢን ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል ጽዱና ከብክለት ነጻ የሆነ አካባቢን ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው
ሀዋሳ ፤ ግንቦት 27/2016(ኢዜአ)በሲዳማ ክልል ጽዱና ከብክለት ነጻ የሆነ አካባቢን ለመፍጠር ከተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ደን፣ አካባቢና አየር ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ከሀዋሳ ኢንደስትሪያል ፓርክና ግሪን ሶፍት ከተሰኘ የሶፍት ፋብሪካ ጋር በመቀናጀት በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የጽዳት ዘመቻና ጉብኝት አድርጓል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽታዬ ዮሙራ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ የሚገኙ ከተሞች ከኢንዱስትሪ ከሚወጡ በካይ ጭስ፣ ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ ብክለት እንዳይደርስባቸው ለማድረግ እየተሰራ ነው።
እንደ ሀገር “ውበት ይንቃ ብክለት ይብቃ” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ባለው ንቅናቄ መሰረት ከተሞችን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ ከብክለት ነጻና ጽዱ እንዲሆኑ ለማድረግ በክልሉ ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
“ኢንዱስትሪዎች ወደ አካባቢ የሚለቋቸው ቆሻሻዎች የተጣሩና ጉዳት የማያደርሱ እንዲሆኑ ከማድረግ አንጻር በሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክና በግሪን ሶፍት ፋብሪካ የሚሰሩ ስራዎች ትልቅ ማሳያ ናቸው” ብለዋል።
ሀዋሳ ከተማ ጽዱና ለኑሮ ምቹ ከተማ እንደሆነች እንድትቀጥል ከማድረግ አንጻር የብክለት መከላከል ስራ ማህበረሰቡ በራሱ መርሃ ግብር ወጥቶለት እየሰራ እንደሚገኝና ይህን አጠናክሮ የመቀጠል ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ማቲዮስ አሸናፊ በበኩላቸው ፓርኩ የሚያመርታቸውን ምርቶች ለውጪ ገበያ የሚያቀርብ መሆኑን ተከትሎ ገዥዎች የፓርኩን ምርት ለመግዛት ያስቀመጡትን ከብክለት የነጻ አገልግሎት መስፈርት መሰረት ያደረገ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
“ኢንዱስትሪያል ፓርኩ በማህበረሰቡ ጤናና በአካባቢው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት የማያስከትል ስራዎችን መስራት ተቀዳሚ ተግባሩ በመሆኑም ከኢንዱስትሪዎቹ የሚለቀቁ ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎች ተጣርተው ከብክለት ነጻ መሆናቸው ሲረጋገጥ ብቻ ነው” ብለዋል።
በዚህም የኢንዱስትሪ ፓርኩ ካለው መሬት ውስጥ 28 ሄክታር የሚሆነው በተለያዩ ተክሎች የተሸፈነ እንደሆነ እንዲሁም ፍሳሽ ቆሻሻን በዚያው በማጣራት መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውልና ዝቃጩን ለግንባታ ስራ የሚውሉ ብሎኬት ለማምረት እንደሚጠቀምበት ገልጸዋል።
በሀዋሳ በሶፍት ወረቀት ምርት ላይ የተሰማራው ግሪን ሶፍት ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሰናይት ዳኜ በበኩላቸው ፋብሪካው ለሚያመርተው ሶፍት በግብዓትነት የሚጠቀመው ከግለሰቦችና ከተለያዩ ተቋማት አገልግለው የሚጣሉ ወረቀቶችን ነው ብለዋል።
ይህን ወረቀት በዓይነት ለይቶ በማጠብና ከቀለም ነጻ በማድረግ ለሶፍት ምርት ከማዋል በተጨማሪ ከፋብሪካው ምንም ዓይነት በካይ ጭስ እንዳይወጣ የሚያደርግ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከአየር ብክለት ነጻ የሆነ አካባቢን ለመፍጠር የሚከናወነውን ተግባር እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለስልጣኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ51ኛ ጊዜ በክልሉ ለ3ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፉን የአካባቢ ጥበቃ ቀን “የመሬት ማገገም በረሃማነትና ድርቅን ለመቋቋም” በሚል መሪ ሀሳብ በሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የጽዳት ዘመቻ በማድረግ አክብሯል።