በአዲስ አበባ የአከራይና ተከራይ ህጋዊ ውል ምዝገባ ሰኔ 1 ቀን 2016 ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የአከራይና ተከራይ ህጋዊ ውል ምዝገባ ሰኔ 1 ቀን 2016 ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2016(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ የአከራይና ተከራይ ህጋዊ ውል ምዝገባ ሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚጀመር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።
የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ በአገሪቱ ያለውን የቤት ኪራይ ችግር ለመፍታት እንዲሁም፣ ፍትሃዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማህበረሰቡ ኑሮና በአጠቃላይ አገራዊ ምጣኔ ሀብት ላይ የሚፈጥረውን ጫና ከግምት በማስገባት ተዘጋጅቶ መጽደቁ ይታወቃል፡፡
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በአዋጁ አስፈላጊነትና አተገባበር ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
በዚሁ ወቅት የቢሮው ሃላፊ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ ከተማ አስተዳደሩ አዋጁን በመመሪያ በማስደገፍ ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅቶቹን እያጠናቀቀ መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህን ተከትሎ ከሰኔ 1 ቀን አንስቶ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓም በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የግል ቤት አከራዮች ከተከራዮቻቸው ጋር ህጋዊ ሰነዶቻቸውን ይዘው በመቅረብ ምዝገባ ማድረግ አንደሚችሉ አስረድተዋል።
ለምዝገባው የሚያስፈልገውን የሰው ሃይልና መሰረተ ልማት በማደራጀት በኩል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
ቤት አከራዮች ህጋዊ የምዝገባ ውል ለመፈጸም ወደ ወረዳ ጽህፈት ቤቶች በሚሄዱበት ወቅት ቤቱ የራሳቸው ስለመሆኑ ወይንም ህጋዊ ተወካይ መሆናቸውን የሚገልጽ ሰነድ ይዘው መቅረብ ይኖርባቸዋል።
ተከራዮች በበኩላቸው ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ ወይንም ሌላ ህጋዊ ማንነታቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ ይዘው መቅረብ እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
በስራ ሰዓት መመዘግብ የማይችሉ አከራይና ተከራዮች ቅዳሜና እሁድ እንዲሁም በስራ ቀን ማታ ከ12 ሰዓት በኋላ ህጋዊ የውል ምዝገባውን መፈጸም እንደሚችሉ ተናግረዋል።
በምዝገባውና አዋጁን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ቅሬታዎችን በመቀበል ለማስተናገድ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው በከተማዋ በህዝብ ውይይት በስፋት ከተነሱ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የቤት ኪራይ ዋጋ መጨመር በመሆኑ ህጋዊ መስመር ለማስያዝ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የቤቶች ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ጸጋዬ ሞሼ አዋጁ አለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ታሳቢ አድርጎ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
አዋጁ የተከራይና አከራይ መብትና ግዴታን በግልጽ ያስቀመጠና የሁለቱንም ወገኖች መብትና ጥቅም በሚዛናዊነት ያስጠበቀ እንደሆነ ገልጸዋል።
በውይይቱ የክፍለ ከተማና ወረዳ አመራሮችን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የተገኙ ሲሆን በአዋጁ ላይ ግልጽነት የሚፈልጉ ጥያቄና አስተያየቶችን አንስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።