በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲያካሂድ የቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምእራፍ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲያካሂድ የቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምእራፍ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላለፉት ሰባት ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲያካሂድ የቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምእራፍ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ።
ኮሚሽኑ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምእራፍ መጠናቀቅን አስመልክቶ ዋና ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ ሰጥተዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በመድረኩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች፣ ሦስቱ የመንግሥት አካላት ተወካዮች፣ የማህበራት እና ተቋማት ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተወካዮች በአምስት ቡድኖች ተከፍለው አጀንዳዎቻቸውን በማሰባሰብ ለኮሚሽኑ አስረክበዋል፡፡
መድረኩ ያለምንም ገደብ በነጻነት መከናወኑንም ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች አጀንዳዎቻቸውን በማቅረብ ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
ኮሚሽኑ በቀጣይ አጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምእራፍ በድሬዳዋ አስተዳደር እና በክልሎች እንዲሁም በፌደራል እና በዳያስፖራ ደረጃ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።
ሂደቱ እንዲሳካ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም ዋና ኮሚሽነሩ ምስጋና አቅርበዋል።