ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የግጭት አዙሪት በምክክር በመቋጨት ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ሁላችንም ልንዘጋጅ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የግጭት አዙሪት በምክክር በመቋጨት ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ሁላችንም ልንዘጋጅ ይገባል ሲሉ በምክክር ምዕራፍ የባለድርሻ አካላት ተወካዮች ገለጹ።

በኢትዮጵያ የቆዩና እየተንከባለሉ የመጡ ሀገራዊ ችግሮችን በጋራ እንፍታ የሚል የምክክር ሃሳብ ተወጥኖ ሂደቱም ሦስተኛው ምዕራፍ ላይ ይገኛል። 

በሂደቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላትና አጠቃላይ የኅብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ታክሎበት ሀገራዊ ምክክሩ በተሳካ መልኩ ቀጥሏል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የፖለቲካ ስትራቴጂ አማካሪ ኢብሳ ነገዎ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር እየተሸጋገሩ ለመጡ ውስብስብ ሀገራዊ ችግሮች ሁነኛ መፍትሔ ስለመሆኑ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የቆየው የፖለቲካ ሥልጣን በአብዛኛው በኃይልና በአፈ-ሙዝ የታገዘ መሆኑን አስታውሰው፤ በዚህም ብዙ ሀገራዊ ውድመት ደርሷል ብለዋል።

በዚህ ዘመን ግን በጠብመንጃ የሚመጣ መፍትሔና የሚገኝ ሥልጣን አለመኖሩን ሁላችንም እርግጠኛ ልንሆን ይገባል ነው ያሉት።

በመሆኑም እየተሸጋገሩ የመጡ ውስብስብ ሀገራዊ ችግሮች በምክክር በዘላቂነት በመፍታት የኢትዮጵያን የግጭት አዙሪት ለመቋጨት ሁላችንም ልንዘጋጅ ይገባል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በሀሳብ የበላይነት በነጻነት ለመወያየት አስቻይ ሁኔታዎች ስላልነበሩ ጦርነት አማራጭ እንደነበር ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ሁሉንም አትራፊ የሚያደርገው የውይይት አማራጭ ብቻ መሆኑን ገልፀዋል።


 

ታዋቂ ግለሰቦችን በመወከል በአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር የተሳተፉት ተሻለ ሰብሮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም፣ ዘላቂ ሰላምና አንድነት ያገባኛል የሚል ዜጋ ከግጭት በመውጣት ምክክርን ብቻ አማራጭ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።

በመሆኑም በሚቀርቡ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት በመመካከር ሀገራዊ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ልንዘጋጅ ይገባል ነው ያሉት።     


 

የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና ልማት ማኅበር ፕሬዝዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ፤  በአገራዊ ምክክሩ ልዩነቶች ላይ በሰከነ መንፈስ በመነጋገር መፍትሔ ማምጣት አለብን ብለዋል።

ሀገር አቀፉ የምክክር ምዕራፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ከቀናት በፊት በይፋ መጀመሩ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም