የኮሪደር ልማቱን ወደ ሌሎች ከተሞች በማስፋት ፍትሃዊ የከተሞች እድገት እንዲኖር እየተሰራ ነው--ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማቱን ወደ ሌሎች ከተሞች በማስፋት ፍትሃዊ የከተሞች እድገት እንዲኖር እየተሰራ ነው--ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2016(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለውን የኮሪደር ልማት ወደ ሌሎች ከተሞች በማስፋት ፍትሃዊ የከተሞች እድገት አንዲኖር እየተሰራ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ ገለጹ፡፡
አገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት በስፋት ካከናወናቸው የልማት ስራዎች መካከል በከተሞች የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሃሳብ አመንጪነት በአዲስ አበባ የተገነቡት የገበታ ለሸገር ፕሮጀክቶች የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባሻገር የተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
አሁን ላይ ደግሞ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ የተመቸች፣ ጽዱና ዘመናዊ ከተማ የማድረግ ውጥን በመያዝ የኮሪደር ልማት ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡
በኮሪደር ልማቱ የመንገድ አውታሮች የማስፋፋት ስራ፣ ዘመናዊ የመብራት ዝርጋታ፣ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች፣ ምቹ የእግረኛና ብስክሌት መንገድ ግንባታ፣ ያረጁ ህንጻዎች ጥገና እና ማስዋብ እየተከናወኑ ይገኛል፡፡
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ፤ የተለያዩ ከተሞች ከአዲስ አበባ የልማት ፕሮጀክቶች ልምድ ወስደው እንዲተገብሩ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት በተጀመረበት ወቅት ከ38 ከተሞች ከንቲባዎችን በማምጣት ልምድ እንዲቀስሙ መደረጉን ጠቅሰው፤ የወሰዱትን ልምድ ከከተሞቻቸው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
የከተሞች እድገት የሀገር ኢኮኖሚ እድገት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ በከተሞች እድገት ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የከተሞችን እድገት ፍትሃዊ ለማድረግም ፎረም በማቋቋም ጭምር እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
መንግስት በአዲስ አበባ ብቻ በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደማይቻል ጽኑ እምነት አለው ያሉት ሚኒስትሯ፤ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ከተሞችን በማልማት ረገድ የተናበበ ስራ እየተከናወነ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡
መንግስት በአሁኑ ወቅት ለከተሞች እድገት የሰጠው ትኩረትም የኢትዮጵያ ከተሞች እንዲነቃቁ ማድረጉንም ነው ያነሱት፡፡