ቀጥታ፡

የሞጆ የአረንጓዴ ሎጅስቲክ ማዕከል የማስፋፊያ ግንባታ በቂ መጋዘን እንዲኖር ከማስቻሉም በላይ ኮንቴነር ማስተናገድ አቅምን በእጥፍ ይጨምራል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2016(ኢዜአ)፦የሞጆ የአረንጓዴ ሎጅስቲክ ማዕከል የማስፋፊያ ግንባታ በቂ መጋዘን እንዲኖር ከማስቻሉም በላይ ኮንቴነር የማስተናገድ አቅምን በእጥፍ  እንደሚጨምር የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ምህረተአብ ተክሉ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የሞጆ ደረቅ ወደብ  ስያሜውን ወደ ሞጆ የአረንጓዴ ሎጅስቲክ ማዕከል በመቀየር ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጋር የማስተሳሰር ስራ እየተሰራ ነው።

በማዕከሉም በተቋሙ በጀት እና ከዓለም ባንክ ጋር በተደረገ የብድር ስምምነት በሁለት መልኩ የማስፋፊያ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተቋሙ በጀትና እቅድ የሚከናወነው የማስፋፊያ ስራ በዋናነት መጋዘኖች፣ ተርሚናሎችን የማስፋትና  አጠቃላይ አገልግሎቱን የማሳለጥ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

በዚህም  5 ሺህ 400 ስኩዌር ሜትር ስፋት ያላቸው ስምንት ትልልቅ መጋዘኖች መገንባታቸውን  ጠቁመዋል። 

ይህም በመጋዘን ጥበት ምክንያት ይከሰት የነበረውን ችግር መፍታቱን ጠቅሰው የተርሚናሎች ኮንቲነር የማስተናገድ አቅም ማደጉንም ተናግረዋል።

ከዓለም ባንክ ጋር በተደረገ ብድር ስምምነት ደግሞ የሚበላሹ ምግብ ነክ ምርቶችን ለመላክ የሚያስችል የቀዝቃዛ መጋዘንን ጨምሮ ሌሎች የማስፋፊያ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህም  የወደቡን አቅም በእጥፍ የሚያሳድግ እንደሆነ ነው ያስረዱት።

አሁን ላይ ጥቅም  ላይ የዋለ 86 ሄክታር ቦታ አለ ያሉት ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚው እየተከናወነ ያለው ማስፋፊያ ሲጠናቀቅ 162 ሄክታር በላይ የለማ ቦታ ይኖራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም