ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት የዜጎችን ሁለንተናዊ ልማትን  ያቀላጥፋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2016(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት የዜጎችን ሁለንተናዊ ልማት  እንደሚያቀላጥፈው በመዲናዋ የተለያዩ  ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ገለጹ።

አዲስ አበባ የዓለም የዲፕሎማሲ መዲና፣ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ከተማ፣ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ እንቅስቃሴ መናኸሪያ መሆኗን ተከትሎ ከተማዋን የሚመጥን የልማት ስራ በሰፊው በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ 

ከነዚህ ስራዎች አንዱ የሆነው የመዲናዋ የኮሪደር ልማት ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ፣ ከአራት ኪሎ እስከ ቦሌ ድልድይ፣ ከቦሌ ድልድይ በመገናኛ ወደ ሲኤምሲ፣ ከቦሌ ተርሚናል ወደ ጎሮ፣ ከሜክሲኮ ወደ ወሎ ሠፈር፣ እንዲሁም ከእንግሊዝ ኤምባሲ ወደ አራት ኪሎ የሚወስዱ ኮሪደሮችን የሚያጠቃልል ነው፡፡

ኢዜአ በመዲናዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር እና የወንዝ ዳር ልማት ሥራዎችን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  እሳትና አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን፣ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ እንዲሁም የመንገዶች ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎችን አነጋግሯል። 

የአዲስ አበባ  እሳትና አደጋ ስራ አመራር የኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር  አቶ ይክፈለው ወልደመስቀል፥ በመዲናዋ በተለያዩ አጋጣሚዎች የእሳት፣ የትራፊክ፣ የመሬት መደርመስ እና የጎርፍ አደጋዎች እንደሚከሰቱ ገልጸዋል። 

የቆሻሻ አወጋገድ፣ የህንፃ ግንባታ አስተዳደር፣ የመንገድ መሰረተ ልማት እና የግንባታ ግብዓት አጠቃቀም ጉድለቶች በመዲናዋ ለሚከሰቱ አደጋዎች ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል። 

በዚህም የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋን ከመከሰታቸው በፊትና በኋላ ለመከላከል ጥናትን መሰረት ያደረገ የቅደመ መከላከልና የፈጣን ምላሽ አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል።

   በመዲናዋ ተግባራዊ እየተደረጉ የሚገኙት የኮሪደር እና የወንዝ ዳር ልማት ስራዎች ወንዞችን ንፁህ ከማድረግ ባለፈ  በወንዞች የውሃ ሙላት ጉዳት የሚያስተናግዱ ዜጎችን  ህይወትና ንብረት  ከአደጋ መታደግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። 

በተለይም የኮሪደር ልማት ስራው መዲናዋን ለነዋሪዎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ምቹ በማድረግ የሚከሰቱ የተለያዩ አደጋዎችን ለመቀነስ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳላቸው አስረድተዋል። 

  

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውብትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የተፋሰስና የአረንጓዴ ልማት ቡድን መሪ ዘነበ በለጠ፥ የኮሪደር እና ወንዝ ዳር ልማት ስራዎች የከተማዋን ጽዳትና ውበት በመጠበቅ ለነዋሪዎቿ እና ጎብኝዎች ምቹ እንቅስቃሴን የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል። 

የወንዝ ዳር ልማት ስራዎቹ ለዜጎች ውብ የመዝናኛ ስፍራን ከመፍጠር ባለፈ አደጋን ለማስቀረት አይነተኛ ሚና አላቸው ብለዋል። 

በኮሪደር ልማቱ የሚሰሩ ደረጃቸውን የጠበቁ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ጤናማ የትራፊክ ፍሰት እንዲፈጠር እድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን የገለጹት በአዲስ አበባ የመንገዶች ባለስልጣን የድልድዮች አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ መላኩ ታደሰ ናቸው። 


 

ግንባታዎቹ ጤናማ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር በማድረግ በሰውና ንብረት ላይ የሚደርስ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ጉልህ ፋይዳ አላቸው ብለዋል፡፡ 

መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ የከተማ ማስዋብና የመናፈሻዎች ፕሮጀክቶችን ሲተገብር መቆየቱ ይታወቃል፡፡

የእንጦጦ መናፈሻ ፣ የአንድነት ፓርክ፣ ወዳጅነት ፓርክ፣ የአራት ኪሎና የመስቀል አደባባይ፣ የቦሌ መንገድ፣ ከአዲስ አበባ ውጪም ሃላላ ኬላ፣ ወንጪ፣ ኮይሻ፣ ጨበራ ጩርጩራ የዚሁ ማሳያ ናቸው ፡፡ 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም