ሀገር በቀል እውቀቶችን ከዘመናዊ ጋር አስተሳስሮ ጥቅም ላይ ለማዋል ማህበረሰቡን ማሳተፍ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር በቀል እውቀቶችን ከዘመናዊ ጋር አስተሳስሮ ጥቅም ላይ ለማዋል ማህበረሰቡን ማሳተፍ ይገባል
አዳማ፣ ግንቦት 27/2016(ኢዜአ) ሀገር በቀል እውቀቶችን ከዘመናዊ ጋር አስተሳስሮ ጥቅም ላይ ለማዋል ማህበረሰቡን ማሳተፍ እንደሚገባ ምሁራን አመለከቱ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ትምህርት ኮሌጅ የሀገር በቀል እውቀቶች መምህርና ተመራማሪ ሰለሞን በላይ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት ሀገር በቀል እውቀቶችን በባለቤትነት ይዘው ያቆዩትን የማህረሰብ ክፍሎች ማካተትና እየጠፉ ያሉትንም መሰነድ እውቀቱን ለማስቀጠል ይረዳል፡፡
ሀገር በቀል እውቀቶች የማይዳስሱት ዘርፍ እንደሌለ የገለጹት ምሁሩ፤ ለወጣቱ የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ የቱሪስት መስህብነት የጎላ ድርሻ አላቸው ብለዋል።
ሀገር በቀል እውቀቶችን በጥናትና ምርምር በመደገፍ ከዘመናዊ እውቀት ጋር በማዛመድ ጥቅም ላይ እንዲውል የተጀመረው እንቅስቃሴ ማህበረሰቡን በማሳተፍ እንዲጠናከር ጠይቀዋል፡፡
ይህም የሀገር በቀል እውቀቶች ማንም የማይደርስባቸው ደሴቶች ብቻ ሆነው በተመራማሪዎችና አጥኚዎች ዘንድ ብቻ መታወቃቸው አብቅቶ የሀገር ሀብት ሆነው ለማስቀጠል እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
ዘርፉ እንደ ኋላቀርና ጎታች ልማዳዊ ድርጊት የሚታይበት አተያይ ቀርቶ ወደ ሀብት፤ የማንነት ገጽታ መገንቢያ እየተለወጠ መምጣቱ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ያመለከቱት ምሁሩ፤ ይህም ብሔራዊ ተቋም ሆኖ እንዲወጣ የምሁራን ብቻ ሳይሆን የዜጎች ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ሥነ ጽሁፍ መምህር የሻው ተሰማ በበኩላቸው የሀገር በቀልና ባህላዊ እውቀቶች ቀዳሚ ባለቤትና ባለጉዳይ የሆነውን ማህበረሰብ ለማሳተፍ የተጀመረው እንቅስቃሴን እድንቀዋል፡፡
ሀገር በቀል እውቀቶች ከአፈር፣ ውሃ፣ ተክሎች፣ ማዕድናት፣ ነፍሳትና ሌሎች የተፈጥሮ በረከቶች የሚያካትቱ፤ መድሃኒትና ጌጣጌጥ የመሳሰሉ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጡ ቁሶችን ለመቀመም የሚያስችሉ የእውቀት ሀብቶችን አምቀው መያዛቸውን ጠቁመዋል፡፡
ማህበረሰቡ የሚያደርገው ተሳትፎ በመርሃ ትምህርት ፤ በትምህርት መርጃ መሳሪያዎችና በፖሊሲ አካቶ ለመተግበር እንደሚያስችልም አመልክተዋል፡፡
በዚህም መጪው ትውልድ ባህላዊ እውቀቶችን ቅርስ አድርጎ እንዲይዝና ለአዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች መነሻ በማድረግ ለራሱ ዘመን አስማምቶ እንዲቀምባቸው ያግዘዋልም ብለዋል መምህር የሻው፡፡
የኢትዮጵያዊ ማንነት መገለጫ የሆኑት የማህበረሰብ እውቀት እንዳይጠፉና በምዕራብ ዘመሙ መጤ ባህል እንዳይበረዙ የመታደግ ግዴታችንን መወጣት አለብን ሲሉም አክለዋል፡፡
በዚህም ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ ለውስን አካባቢዎች ከሚሰጠው ጥቅም አልፎ ለሀገር ጥቅም እንዲውል መስራት እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የባህል እሴቶችና ሀገር በቀል እውቀቶች መሪ ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ እስከዳር ግሩም በበኩላቸው የኢትዮጵያን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ከሚያጎለብቱ እሴቶች አንዱ ትውልዱን በሀገር በቀል እውቀቶች ተጠቃሚና ባለቤት ማድረግ ነው ይላሉ፡፡
በባህላዊ የመድሃኒት ቅመማ እውቀቶቻቸውን በዓለም በምሳሌነት መጥቀስ የቻሉትን የቻይናና የህንድን ተሞክሮ ብንመለከት በዘርፉ ያልተነካ እምቅ ሀብታችን ለዓለም የሚተርፍ መሆኑን አስተውለናልም ብለዋል፡፡
ትውልዱ ከልጆች አስተዳደግ ጀምሮ ኢትዮጵያዊ ማንነት ሳይሸረሸር የሚያቆዩ እሴቶችን በማስጠበቅ ማንነቱን እንዲወርስ ምሁራን ብቻ ሳይሆኑ፣ዜጎች እንረባረብ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሀገር በቀል እውቀቶች ፎረም ምስረታ በአዳማ ከተማ ማካሄዱ ይታወሳል።