ቀጥታ፡

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የፍራፍሬ ችግኝ ሳይንሳዊ ይዘቱን ተከትሎ በኩታ ገጠም ይተከላል

አዳማ ፤ ግንቦት 27/2016(ኢዜአ)፦በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የፍራፍሬ ችግኝ ሳይንሳዊ ይዘቱን በጠበቀ መንገድ በኩታ ገጠም ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።

የፍራፍሬ ችግኝ ተከላው ሳይንሳዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ በኩታገጠም እንዲተከል ለማስቻል የሚመክር መድረክ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በግብርና ሚኒስቴር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ፀሐፊ አቶ ፋኖሴ መኮንን እንደገለፁት፤ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለፍራፍሬና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ላላቸው ዛፎች ትኩረት ተሰጥቷል።

የመድረኩ ዓላማም ፍራፍሬን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ዛፎች በተቀናጀ መልኩ በኩታ ገጠም ለመትከል ተገቢውን ዝግጅት ከወዲሁ ለማድረግ ነው ብለዋል።

ለዘንድሮው ተከላ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ችግኞች ዝግጅት በመካሄድ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተከላው በተለይም በአባይ ተፋሰስ አካባቢ ትኩረት ተደርጎ እንደሚከናወንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም በሁሉም ተፋሰሶች አካባቢያዊ ስነ ምህዳርን ያማከለ ተከላ ይከናወናል ነው ያሉት።

በተመሳሳይ በከተሞች አካባቢም የውበትና የፍራፍሬ ችግኞች በትኩረት ይተከላሉ ብለዋል።

በሚኒስቴሩ የሆርቲ ካልቸር መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ አብደላ ነጋሽ በበኩላቸው፤ የፍራፍሬ ችግኞች ምርታማነትን ለማሳደግ የሚባዙ  ችግኞች ተከላ ሳይንሳዊ ይዘታቸውን መጠበቅ አለበት ብለዋል።

ገበያን መሰረት አድርጎ በኩታገጠም ዘዴ ልማቱን በማከናወን የኢንዱስትሪ ግብዓት ፍላጎትን ለሟሟላት እንዲቻል ግብ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም ከችግኝ ዝግጅት ጀምሮ የፍራፍሬ ችግኝ የጉድጓድ ዝግጅት በተለየ መልኩ እንዲከናወን ተገቢውን ዕውቀትና ክህሎት ለማስጨበጥ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።

ለምግብነት አገልግሎት የሚውሉ የፍራፍሬ ዝርያዎች በተለይ አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ቴምር፣ ፓፓያ፣ ማንጎና ሌሎች ችግኞችን በኩታ ገጠም ለማልማት  ነው ብለዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተከላ ቦታና የጉድጓድ ዝግጅት አንፃር የተሻለ ክንውን መኖሩን የጠቀሱት ደግሞ በኢትዮጵያ ደን ልማት ኢንስቲትዩት የአረንጓዴ ልማትና ሰው ሰራሽ ደን መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ አበሩ ጠናው ናቸው።

ችግኙ እንዲፀድቅ የጉድጓድ ዝግጅት ወሳኝ ሚና አለው" ያሉት አቶ አበሩ፤ የእስከ አሁኑ የጉድጓድ ዝግጅት በቂ ባይሆንም የተሻለ ነው ብለዋል።

የደን፣ የውበትና የፍራፍሬ ችግኞች የተከላ ቦታ በሚሰጡት አገልግሎትና አንደ አየር ፀባይ ተለይተው ወደ ቦታው እንዲጓጓዙም ከወዲህው ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም