በሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው የተጻፈው "የጀግንነት ሥነ-ልቦና" የተሰኘው መጽሐፍ ግንቦት 30 ይመረቃል - ኢዜአ አማርኛ
በሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው የተጻፈው "የጀግንነት ሥነ-ልቦና" የተሰኘው መጽሐፍ ግንቦት 30 ይመረቃል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2016(ኢዜአ)፦ በሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው የተጻፈው "የጀግንነት ሥነ-ልቦና" የወታደራዊ ሥነ-ልቦና መጽሐፍ በመጪው ዓርብ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ይመረቃል።
የመጽሐፉን ምርቃት በማስመልከት የተቋቋመው ኮሚቴ ዛሬ በስካይ ላይት ሆቴል መግለጫ ሰጥቷል።
ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው ከመሠረታዊ ወታደርነት እስከ ከፍተኛ ጄኔራል መኮንንነት በታማኝነትና ቅንነት በተለያዩ ኃላፊነቶች እያገለገሉ የሚገኙ ናቸው።
ጄኔራል መኮንኑ በማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም የመጀመሪያ ዲግሪ፣ እንዲሁም በሊደርሺፕና መልካም አስተዳደር የሁለተኛ ዲግሪ አላቸው።
በወታደራዊ ትምህርት ካዴት፣ ስታፍ ኮሌጅ፣ እንዲሁም በስዊድን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የወታደራዊ ስታፍን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ከፍተኛ የአመራር ኮርስ ወስደዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዳርፉር ሰላም ማስከበር ሴክተር ሦስት የዘመቻ ኃላፊ፣ የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የዘመቻና የመረጃ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል።
በአጠቃላይ ለ30 ዓመታት በዘለቀው የወታደራዊ ኃላፊነታቸው ከተዋጊነት እስከ አዋጊነት በማገልገል በሰሜኑ ጦርነት በነበራቸው የጎላ አበርክቶ ምርጥ የዘመቻ መኮንን ሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በአገልግሎት ዘመናቸውም የአምስት፣ የአሥር፣ የ15፣ 25 እና የ30 ዓመት አገልግሎት ሜዳሊያና ኒሻን ተሸላሚም ናቸው።
በቅርቡ አልሸባብ ኢትዮጵያን ለማተራመስ በምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል ያደረገውን ሙከራ በመሪነት ማክሸፍ ችለዋል።
ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው ከዚህ ቀደም "Leadership challenge managing the causes of conflict between Geri and borena" ጽፈዋል።
በ11 ምዕራፎች የተቀነበበው የጀግንነት ሥነ-ልቦና መጽሐፍ በአማርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ሶማሊኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ነው።
አቀራረቡም ከታሪካዊ ሥነ-ልቦና ዳሰሳ እስከ ንድፈ-ኃሳባዊ መርሆዎች የወታደራዊ ሥነ-ልቦናን አተገባበር ይተነትናል።
መጽሐፉ የሥነ-ልቦና ጦርነትን የኢትዮጵያ ወታደራዊ አደረጃጀት በምን መልኩ መጠናከር እንዳለበት ምክረ-ኃሳብም ያቀርባል።
በ11ዱ ምዕራፎች የወታደራዊ ሥነ-ልቦና ምንነት፣ ወታደራዊ ጀግንነት፣ ወታደራዊ ሳይንስ፣ የጦርነት ሥነ- ልቦና ዝግጅት፣ የወታደራዊ አመራር ጽንሰ-ኃሳብና የተግባር አመራር በዝርዝር ቀርበውበታል።
በተጨማሪም በወታደራዊ ሥልጠና ላይ ቅሬታን የማስወገድ ስልቶችና ወታደራዊ ግምገማ ምን እንደሚመስል ያብራራል።
በአጠቃላይ ከውጊያ በፊት፣ በውጊያ ወቅትና በኋላ ሊኖር የሚገባውን የጀግንነት ሥነ-ልቦና ዝግጅትና ወኔ በዝርዝር ያስረዳል።
ከመጽሐፍ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ለእናት ሀገራቸው ዳር ድንበር መከበር አካላቸውን ላጡ ጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆች ድጋፍ የሚውል ይሆናል።