ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ትብብራቸውን የሚያጠናክር ምክክር አካሄዱ  

አዲስ አበባ፤ግንቦት 27/2016(ኢዜአ) የኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክን የፋይናንስና ኢኮኖሚ ትብብር የሚያጠናክር ምክክር መካሄዱ ተገለጸ።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የኮሪያ ሪፐብሊክ ኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ምክትል ሚኒስትር ኪም ቢያንግ ህዋን ጋር ተወያይተዋል። 

በውይይቱ ወቅት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ የኮሪያ ሪፐብሊክ እና ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናትን የተሻገረና በደም የተሳሰረ ወዳጅነት እንዳላቸው አውስተዋል።


 

ሀገራቱ በቀጣይ አራት ዓመታት ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የፈረሙት የ1 ቢሊዮን ዶላር የፋይናንስ ማዕቀፍ ስምምነትም ትልቅ እመርታ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ በወሰደቻቸው ርምጃዎች የተገኙ ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን ያስረዱት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ካላት ሰፊ የሰው ሀብትና ምቹ የስራ ከባቢ አንጻር ግንኙነታቸውን አጠናክረው መቀጠል እንደሚስፈልግ ገልጸዋል።

በተለይም በኢኮኖሚና ፋይናንሱ ዘርፍ ኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ ያላቸውን ጠንካራ ግንኙነት ለማላቅ በትኩረት እንደሚሰራ ነው የገለጹት።

የኮሪያ ሪፐብሊክ ኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ምክትል ሚኒስትር ኪም ቢያንግ ህዋን በበኩላቸው የሁለቱን ሀገራት የፋይናንስ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በዚህም ኮሪያ ሪፐብሊክ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላት ጠቁመዋል።

አጋርነታቸውን ለማሳደግ በኢኮኖሚያዊ ትስስር ማዕቀፍ ውስጥ የባለብዙ ወገን ትብብር ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረውም መናገራቸውን በሴኡል የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም