የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ የአከራይና ተከራይ መብቶችን በሚዛናዊነት ያስቀመጠ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2016(ኢዜአ)፦የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ የአከራይና ተከራይ መብቶችን በሚዛናዊነት ያስቀመጠ ነው።

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1320/2016 ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የቤቶች ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ጸጋዬ ሞሼ አዋጁ አለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ታሳቢ አድርጎ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

መሪ ስራ አስፈጻሚው የአዋጁን ይዘት፣ አስፈላጊነት፣ አተገባበርና ሌሎች ድንጋጌዎችን በተመለከተ ለውይይቱ ተሳታፊዎች  ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በተመሳሳይ በአከራይና ተከራይ መካከል ስለሚደረግ ውል ይዘት፣ ግዴታና መብት፣ የቤት ኪራይ ክፍያ የሚፈጸምበትን ዘዴ፣ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውልና ዋጋ፣ የተቆጣጣሪ አካል ሀላፊነትና ሌሎች የአዋጁ ድንጋጌዎችን በዝርዝር አቅርበዋል።

የመኖሪያ ቤት ኪራይን በመቆጣጠር የአከራይንና ተከራይን ጥቅም ሚዛን የሚያስጠብቅ ማዕቀፍ በማውጣት ለችግሩ መፍትሄ መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ አዋጁ እንዲወጣ መደረጉን ጠቁመዋል።

አዋጁ በአገሪቱ ያለውን የቤት ኪራይ ችግር፣ ፍትሃዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማህበረሰቡ ኑሮና በአጠቃላይ አገራዊ ምጣኔ ሀብት ላይ የሚፈጥረውን ጫና ከግምት በማስገባት መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

ማንኛውም የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ሲገባ አከራይ ከተከራይ ሊጠይቅ የሚችለው ቅድመ ክፍያ ከሁለት ወር የቤቱ ኪራይ ዋጋ ሊበልጥ እንደማይችል አዋጁ ያስቀምጣል።

ተከራይ የውል ስምምነትን በተደጋጋሚ ከጣሰ፣ የአካባቢን ሰላም የሚያውክና ሌሎች ከስነ-ምግባር ውጭ የሆኑ ባህርያትን ካሳየ ቤቱን ለቆ ሊወጣ እንደሚችል ተደንግጓል።

አዋጁ የቤት ኪራይ ክፍያ ስርአትን የደነገገ ሲሆን የቤት ኪራይ በባንክ ወይንም በሌላ የኤሌክትሮኒክ የክፍያ ዘዴ ብቻ እንዲፈጸም ያስገድዳል።

ይህም በጥሬ ገንዘብ ክፍያ በመፈጸም የሚፈጠርን ማጭበርበር በመቀነስ አዋጁ የታለመለትን አላማ ለማሳካት እንደሚያስችል ነው የተገለጸው።

እንደ አስተዳደሩ ነባራዊ ሁኔታ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደርን በተለይም የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውልንና ዋጋን የሚከታተልና የሚያስፈጽም አካል ወደ ስራ እንዲገባ ማድረግ ከከተማ አስተዳደሩ ይጠበቃል።

በውይይቱ የክፍለ ከተማና ወረዳ አመራሮችን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የተገኙ ሲሆን በአዋጁ ላይ ግልጽነት የሚፈልጉ ጥያቄና አስተያየቶችን አንስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም