ቀጥታ፡

የነቀምቴ ኤርፖርት በቅርቡ ሥራ ለመጀመር ዝግጁ መሆኑ የመንግሥትን የልማት ቁርጠኝነትና የመፈፀም አቅም በተግባር ያሳየ ነው

ነቀምቴ፤ ግንቦት 27/2016(ኢዜአ)፦ የነቀምቴ ኤርፖርት ግንባታ ተጠናቆ ሥራ ለመጀመር ዝግጁ መሆኑ የመንግሥትን የልማት ቁርጠኝነትና የመፈፀም አቅም በተግባር ያሳየ መሆኑን የነቀምቴና አካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።

መንግሥትን በመደገፍ የወለጋ ዞኖች ነዋሪዎች በነቀምቴ ከተማ ባደረጉት ሰልፍ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በዚሁ ሁነት ላይ በመገኘት ባስተላለፉት መልዕክት የሕዝቡን ዘላቂ ሰላም በማፅናት የልማት ፍላጎቶችንም ለማሳካት መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም የወለጋ ዞኖች ነዋሪዎች ለልማት ለሰላምና አንድነት ልዩ ትኩረት በመስጠት እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲሰሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

መንግሥት ሰላምን ከማረጋገጥ በተጓዳኝ የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የነቀምቴ ኤርፖርት ግንባታ መፋጠንና ሥራ ለመጀመር ዝግጁ መሆኑም የዚሁ የልማት ስኬት ማሳያ ነው።

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ነቀምቴ በረራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን ኢዜአ ቀደም ሲል መዘገቡ ይታወሳል።

አየር መንገዱ የውጭ ሀገራት የበረራ መዳረሻዎችን ከማስፋት ባለፈ እያደገ የመጣውን የሀገር ውስጥ የደንበኞች ፍላጎት ለማሳካት እየሰራ ነው።

በዚህም መሠረት ወደ ነቀምቴ በረራ ለማስጀመርና በሳምንት አራት ጊዜ ለመብረር ዝግጅቱን አጠናቋል።


 

በነቀምቴ ከተማና አካባቢው ኢዜአ ካነጋገራቸው መካከል አቶ ሚደቅሳ አለሙ፤ የአየር መንገዱን በረራ መጀመር በጉጉት እየተጠባበቁ መሆኑን ገልፀዋል።

የኤርፖርቱ ግንባታ በፍጥነት መጠናቀቅ የመንግሥትን የልማት ቁርጠኝነትና የመፈፀም አቅምን በተግባር ያሳየ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለምስራቅ ወለጋ እና አካባቢው ትልቅ የምስራች መሆኑንም ተናግረዋል።


 

አቶ ገመቹ ኦብሳ በበኩላቸው፤ የነቀምቴ ኤርፖርት ሥራ መጀመር ሕዝቡ ለረዥም ዓመታት በጉጉት ሲጠብቀው የነበረ ነው ብለዋል።

የአየር መንገዱ ሥራ መጀመር ለኢኮኖሚ ልማትና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የላቀ ሚና እንደሚኖረውም አንስተዋል።


 

አቶ ፈይሳ ሊኪሳ እና አቶ ተመስገን ገቢሳም እንዲሁ፤ መንግሥት በገባው ቃል መሠረት እየፈፀመ በመሆኑ ትልቅ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።

በመሆኑም በወለጋ ዞኖች መንግሥት ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት ይበልጥ ለማገዝ ተዘጋጅተናል ሲሉም አረጋግጠዋል።

የነቀምቴ-ቡሬ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ዳግም የተጀመረ ሲሆን ከአንዶዴ - አገምሳ እና ከአገምሳ ቡሬ ያለው ግንባታም በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም